Hiber Radio: ፋሽስት ወያኔ የአማራ ገበሬ ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻውን ጀምሯል!-አቻምየለህ ታምሩ

የፋሽስት ወያኔ የመንፈስ አባት ፋሽስት ጥሊያን ኢትዮጵያን እንደተቆጣጠረ ከሁሉ አስቀድሞ ያደረገው ነገር ቢኖር የኢትዮጵያን አርበኞች ያዳክማል ያለውን የትጥቅ ማስፈታት ዘመቻ ማካሄድ ነበር። በርግጥ ከወረራው በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደገና ሲቋቋም መሳሪያ የፈለገ ሁሉ የመሳሪያ ባለቤት እንዲሆን የመሳሪያ መደብር ተከፍቶ በፋሽስት ጥሊያን መሳሪያውን የተቀማ ኢትዮጵያዊ የመሳሪያ ባለቤት እንዲሆን ተደርጓል። ኋላ ላይ ግን የሲቪየት ሕብረት ተቀጥላ የሆነ ጸረ ኢትዮጵያ አገዛዝ በነመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጀሌነት አዲስ አበባ ውስጥ ሲቋቋም አድሃሪ በተባሉት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ራሱን እንዲከላከልና መብቱን እንዲያስከብር መሳሪያ እየገዛ የታጠቀው የኢትዮጵያ ገበሬ መሳሪያ እንዲፈታና የነበረው መብቱ ሁሉ እንዲቀማ ተደረገ።

ከደርግ ቀጥለው የፋሽስት ጥሊያን የመንፈስ ውላጆች የሆኑት የተከዘ ማዶ የባንዳ ልጆች ፋሽስት ወያኔዎችም ሻዕብያን ተከትለው አዲስ አበባ እንደገቡ መሳሪያ የሌለውን ምስኪን የአማራ ገበሬ ሳይቀር እያነቁ ጠባብ ማሰቃያ ቤት ውስጥ በማጎር የነበረችውን ራሱን የመከላከያ መንገድ ሳይቀር አራቁተው ባርያ አድርገው እየገዘገዙት ይገኛሉ።

በፋሽስት ወያኔ ዘመን በተለይ አማራው በብዛት በሚኖርባቸው አካባቢዎች ያደግን የገበሬ ልጆች ሁሉ እንደምናስታውሰው ፋሽስት ወያኔ በየአካባቢያችን ባሉ የቀበሌ ገበሬ ማህበራት ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ በእርሻ ሲደክሙ የዋሉ አባቶቻችንን ማታ ማታ «ትፈለጋለህ» እያሉ እየወሰዱ «የደበቃችሁትን መሳሪያ አውጡ» በማለት በስራ ሲደክም የዋለ የአባቶቻችንን ባዶ እግር በጽድ ዝንጣፊ ገልብጠው ሲገርፉት ያሰሙት የነበረውን የሲቃ ጩኸት መቼም የምንረሳው አይደለም። ይህንን አይነት የስቃይ ዘመቻ «አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ» ያሉትን የግድያ አዋጅ ተገን አድርገው ፋሽስት ወያኔዎች ከሰሞኑ ደግሞ የመጨረሻ ያሉትን የአማራ ገበሬዎችን ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻ ጀምረዋል።

ፋሽስት ወያኔ የባለፈውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተገድን አድርጎ አማራ በሶስት ዙር ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻ ጀምሮ እንደነበር ይታወሳል። በባለፈው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፋሽስት ወያኔ በመጀመሪያ ዙር ትጥቅ ለማስፈታት የወሰነው «የአማራ ልዩ ኃይል» የሚባለውን ነበር። የአማራ ልዩ ኃይል አባለት ከሆኑት መካከልም በቅድሚያ ትጥቅ እንዲፈቱ የተወሰነባቸው የአማራ ተጋድሎ ሲካሄድ «ግደሉ» የሚል ተልኮ ተሰጥቷቸው «ወገናችንን አንገድልም!» በማለት የሕዝብ ወገን መሆናቸውን ያስመሰከሩት ሕዝብ አክባሪዎችን ነበር።

«የአማራን ልዩ ኃይል» የሚባለውን አካል ትጥቁን ካስፈታ በኋላ የቀጣዩ ዙር ኢላማ የአማራ ሚሊሻዎች ወይንም በተለምዶ «ጉጅሌ» የሚባሉት ነበሩ። በሶስተኛ ዙር ትጥቅ እንዲፈታ ሊደረግ የነበረው የአማራ ገበሬ ነበር። ሆኖም ግን በእቅዳቸው መሰረት በሶስተኛ ደረጃ ትጥቃቸውን እንዲፈቱ የተደረጉት የአማራ ገበርዎች በቀላሉ ትጥቅ የሚፈቱ ስላልሆኑ የማስፈታቱ ጉዳይ ለጊዜው በይደር የተተወ ነበር።

አሁን ግን በድጋሚ ያወጁትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ሶስተኛውንና የመጨረሻ ዙር ያሉትን የአማራ ገበሬን ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻን ተያይዘውታል። የዚህ ዘመቻ ግንባር ቀደም አዝማች የሕወሓቱ ነውረኛ ድርጅት ብአዴን ነው። ነውረኛው ብአዴን በየአካባቢው ያሰማራቸውን የራሱን ሰዎች «ግንባር ቀደም ሰልጣኝ አመራሮች» የሚል የዳቦ ስም ሰጥቶ በየቀበሌው የጦር መሳሪያ ገፈፋ እያካሄደ ነው። በርግጥ ይህ ዘመቻ በተለይም በጎጃምና በጎንደር ቀላል አልሆነላቸውም። የቴዎድሮስ ልጆች እጃቸውን ለጠላት እንደማይሰጡ በአቤ ጉበኛ ቅዬ በአቸፈርና በገብርዬ አምባ በደብረ ታቦር የተፈጠሩ ጀግኖቻችን አስመስክረዋል። የተቀረውም የአማራ ገበሬ የነዚህን ሁለት ጀግኖች ፈለግ በመከተል የቴዎድሮስ ልጅነትን እንደሚያስመሰክር አይጠረጠርም።

ይታያችሁ! የፋሽስት ወያኔ የትግራይ የአፓርታይድ አገዛዝ የአማራን ገበሬ መሳሪያ የሚገፈው የትግሬን ገበሬ በነፍስ ወከፍ እስካፍንጫው አስታጥቆ ነው። የትግራይ ገበሬ ደግሞ የታጠቀው በኢትዮጵያ ሃብት ፋሽስት ወያኔ የገዛውን መሳሪያ ነው።

እንግዲህ! የትግራይ ገበሬ በኛ ሃብት የተገዛን መሳሪያ እስካፍንጫው አስታጥቀው የአማራን ገበሬ በራሱ ሃብት የገዛውን የራሱን መከላከያ እየገፈፉ ራሱን እንዳይከላከል ከማድረግ በላይ ጥቃትና የአፓርታይድ አገዛዝ የለም። ይህ ጥቃት እየተካሄደበት ያለው የአማራ ገበሬ የታጠቀውን መሳሪያ ለጠላት ከማስረከብት በገንዘቡ የገዛውን የግል ንብረቱ የሆነውን የራሱን መከላከያ እየያዘ ራሱን በየ አካባቢው በማደራጀት ሊያጠፋው የተነሳውን ፋሽስት ወያኔንና ጀሌዎቹን ታግሎ ልክ እንዳሜሪካኖቹ ባገሩ ራሱን የሚከላከልበት መሳሪያ የመታጠቅ መብቱን ማስከበር አለበት።

ፋሽስት ወያኔ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቶ የዘመተው በአማራ ገበሬዎች ላይ ብቻ አይደለም። ባለፈው ሰሞን የሕወሓት ነውረኛው ብአዴን መዘገብኋቸው ካላቸው ሶስት መቶ ሃምሳ ሺህ የአማራ ነጋዴዎች መካከል የሃምሳ ሺውን ፍቃድ መሰረዙን ነግሮናል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አይደለም አንድን ዘር ያነጣጠረ በሃገር ደረጃ የሃምሳ ሺህ ነጋዴዎች ፈቃድ ተሰርዞ አይታወቅም። ይህ የዘር መድሎ በፋሽስት ጥሊያኗ ኢትዮጵያም ሆነ በአፓርታይዷ ደቡብ አፍሪካ አልታየም። ይህ የአማራ ለጋዴዎች ላይ የታወጀ የፋሽስት ወያኔ ጸረ አማራ ጦርነት ነው። ይህ የንግድ ፍቃዳቸው የተሰረዘባቸው ሃምሳ ሺ የአማራ ነጋዴዎች በአገራቸው ሰርተው እንዳይኖሩ የተከለከሉና አገራቸውን የተነጠቁ የብዙ መቶ ሺህ ቤተሰብ አሳዳሪዎች ናቸው።

ይህ በፋሽስት ወያኔ አገር አልባ የተደረገው ሃምሳ ሺህ ፍቃዱ የተሰረዘ የአማራ ነጋዴ የአገሩ ባለቤት እንዲሆን ከፈለገ በእድሉ ማማረሩን ትቶ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መሳሪያውን ላለመቀማትና መብቱን ላለማስደፈር ዱር ቤቴ ያለውን የአማራ ገበሬ ትግል መቀላቀልና የግፍ ዘመናችንን ለማሳጠር ቆርጦ መነሳት አለበት። መብቱንና አገሩን የተቀማው ሃምሳ ሺው የአማራ ነጋዴ እድል ስለሌለው ወይንም እግዚያብሔር ስላልፈቀደ በመሆኑ የመጣ እንደሆነ ማሰቡብ ማቆም አለበት። በሃምሳ ሺው የአማራ ነጋዴ የደረሰው በሚሊዮን አማሮች ባለፉት ሀያ ሰባት አመታት ፋሽስት ወያኔ ሲያደርሰው የነበረው አማራን የማዳከምና የማጥፋት አካል ነው። እግዚያብሔር አማራውን ለይቶ ሊጎዳ አይችልም። አማራ ከሌላው በተለየ በአገሩ ሰርቶ እንዳይኖር የተደረገው የአማራን መከራ የድሎቱ ምንጭ ያደረገ የፋሽስት ወያኔ አገዛዝ በመስፈኑ ነው። ስለዚህ መፍትሔው ይህንን ጨካኝ ፋሽስታዊ የባዕድ አገዛዝ መፋለም እንጂ በየ ቤተ እምነቱ እየሄዱ እግዚያብሔርንና አላህን ማማረር አይደለም።

እንደ እውነቱ ከሆነ ፋሽስት ወያኔን ለማስወገድ በቀጥታ መብቱን ተገፎ አገር አልባ የሆነው ሃምሳ ሺህ የአማራ ነጋዴ ትግል ብቻ ከበቁ በላይ ነው። ዛሬ እየገደሉን ያሉት ፋሽስት ወያኔዎችኮ የትግራይን ሪፑብሊክ ለመመስረት ጫካ የገቡት ሰባት ሆነው ነው። የትግል ስኬት የሚወሰነው በመምረርና ባለመምረር ብቻ ነው። ፋሽስት ወያኔ አንድ ባንድ እየበላን ያለው ባንድ ላይ መምረር ባለመቻላችን ነው።

ስለሆነም ባገሩ ሰርቶ እንዳይኖር የተደረገው ሃምሳ ሺህ የአማራ ነጋዴና የትግራይ ገበሬ እስካፍንጫው ታጥቆ የራሱን መለላከያ ትጥቅ እንዲፈታ የተደረገውን የአማራ ገበሬ ተቀናጅቶ በየ አካባቢው ትግል በማድረግ አካባቢውን ከፋሽስት ወያኔ ነውረኛ ድርጅት ከብአዴን ከተላላኪዎች ነጻ አውጥቶ ራሱን በማስተዳደር የአገሩ ባለቤት መሆን መጀመርና ገበሬውን እርሻውን ነጋዴም ንግዱን በነጻነት የሚከውንበት መሰረት መጣል አለበት። ፋሽስት ወያኔን ያገነነው መብታችንን እየተቀማን፣ ሕይወታችንን እየነጠቁ፣ መሬታችንን እወረሩ ዝም ብለን ማየታችን ነው።

ስለዚህ ሰርቶ እንዳይኖር ፈቃዱ የተሰረዘበት ሃምሳ ሺህ የአማራ ነጋዴና የራሱን መለላከያ ትጥቅ እንዲፈታ የተደረገውን የአማራ ገበሬ የአገሩ ባለቤት ለመሆንና መብቱን ለማስከበር ከፈለገ መብቱን ለማስከበር ራሱ ከመታገል በስተቀር ከውጭ መጥቶ መብቱን የሚያስከብርለት አካል እንደሌለ በማወቅ መንገድ ፈልጎ ጣምራ ፈጥሮ በፋሽስት ወያኔና ተላላኪዎቹ የተቀማውን መብቱን ለማስመለስ አካባቢውን ነጻ የማውጣት የራሱን አስተዳደር የመዘርጋት እርምጃ ሳይውል ሳያድር መውሰድ አለበት። ከዚህ ውጭ ያለው አማራጭ በፋሽስት ወያኔ እየተመተሩ መኖር ብቻ ነው።

 Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ  5639993994 ወይም 563999-3988 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596  በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *