Hiber Radio: የዶ/ር አብይ ሹመትና የሙሴ በትር የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ያሬድ ኃይለማርያም ጥሪ

ዶ/ር አብይ አህመድ ቀጣዩ ጠ/ሚ ሆነው የመመረጣቸው ነገር በብዙዎች ዘንድ ቀድሞ የተገመተም ቢሆን በሰበር ዜና መልክ ስሰማ ደስታና ስጋት የተቀላቀለበት ስሜት ተሰምቶኛል። ደስታዮ ከሁለት ምክንያቶች የመነጨ ነው። የመጀመሪያው የህውሃት ግትርነትና ማናለብኝ ባይነት በሕዝብ ትግል፤ በተለይም ቄሮዎች ባደረጉት ትንቅንቅ እና በከፈሉት ከፍ ያለ መስዋዕትነት ሲሰበር ማየቴ ነው። ይህ ድል ላለፉት ሦስት አመታት በዋናነት በኦሮሚያ ክልል፤ እንዲሁም በአማራ ክልል እና የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የታየው የሕዝብ ቁጣና ያላባራ ተቃውሞ ያስከተለው ውጤት ነው። ሁለተኛው ደግሞ የዶ/ር አብይ ስብዕና ነው። ቸኮልክ አትበሉኝና ዶ/ር አብይ ካሳለፍናቸው ሁለት ጠ/ሚንስትሮች ጋር ሲወዳደሩ ያላቸው እውቀት፣ ልምድና የሥራ ተመክሮ፤ በዋነኝነት ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ያላቸው ምልከታ የሁላችንንም ቀልብ የሳበ ነው። በመሆኑም ምንም እንኳን እንደ ኢህአዴ ካለ እኩይና የከሸፈ ድርጅት ውስጥ ቢመጡም ከእንክርዳድ መሃል የተገኙ ምርጥ ፍሬ መስለው ነው የሚታዩኝ። ዙሪያቸውን የከበቧቸው እንክርዳዶች ሳስብ ደግሞ ስጋት ይሰማኛል።

ስጋቴም እንዲሁ ከሁለት ምክንያቶች የመነጨ ነው። የመጀመሪያው በዙዎች እንደሚሉት ወያኔ እኚህን ሰው በጠ/ሚ ማዕረግ ያስቀመጣቸው ቀጣዩን መንገዱን በማስላት ብቻ ከሆነ ነው። ይህውም ግለሰቡ በነጻነት እንዳይሰሩ ቀፍድዶና ባሉት መቃቅሮች አሳስሮ ያላቸውን የሕዝብ ቅቡልነትና ድጋፍ በመጠቀም አሁን ከተጋረጠበት አደጋ እንዲታደጉት የፖለቲካ ቁማሩን አስልቶ ከሆነ የሕዝብ ጥያቄና የሥርዓቱ ምላሽ ‘ፍየል ወዲያ ቅምዝምዝ ወዲህ’ አይነት ስለሚሆን በአገር ላይ ያንዣበበውን አደጋ የከፋ ያደርገዋል። ሁለተኛው ስጋቴ ደግሞ ዶ/ር አብይ ሙሉ ሥልጣናቸውን ይህን የተበላሸና ተወላግዶ በቅሎ ተወላግዶ ያረጀን ሥርዓት ለማነጽና የጎበጠውን ለማቃናት ያዋሉት እንደሆን ነው። ይህ ሥርዓት በእኔ እይታ ተጠጋግኖም እንኳን መቀጠል የማይችል፤ እድሜውን አገባዶ በሞት አፋፍ ላይ እንዳለ ሰው ሆኖ ነው የሚታየኝ። በዚህ አይነት ደረጃ ላይ የደረሰን ሰው ሞት ላይቀር በስቃይ ውስጥ እንዳያልፍ እገዛ ይደረግለታል እንጂ አይቀሬውን ሞት አይታደጉትም። ከዚህ በፊት ‘ሲያልቅ አያምር፤ የሥር ዓቱን ሞት ያሳምርልን’[1] በሚለው ጽሑፌ ለሥርዓቱ የተመኘሁት ይህንኑ ሥቃይና ደም መፋሰስ ያላስከተለ ሽኝትን ነው።

ዶ/ር አብይ የተላበሱትን ቅንነት፣ ለአገርና ለወገን በጎ አሳቢነትና ተቆርቋሪነት፤ እንዲሁም ስለ ኢትዮጵያ ያላቸውን ታላቅ ራእይን ሳስብ የእኚህ ሰው ሥልጣን መያዝ የሙሴን በትር አስታወሰኝ። የእስራኤልን ሕዝብ ከምድረ ገጽ ሊያጠፋ እሳት ጎርሶ የተነሳው ፈርኦን ስድስት መቶ የተመረጡ ሰረገሎችን እና የግብጽን ፈረሶች ይዞና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊቱን አሰልፎ ሲያሳድዳቸው ሙሴ ከአምላኩ ባገኘው ኃይል እጁን ወደ ባህሩ በመዘርጋትና በትሩን በማንሳት የቀይ ባህርን ለሁለት ከፍሎ እስራኤላዊያንን አሻግሮ እንደታደጋቸው ቅዱስ መጽሐፉ ይነግረናል። የኢትዮጵያ ሕዝብም የከፋ ድህነት፣ አይን ያወጣ ሙስና እና ዝርፊያ፣ መረን የለቀቀ የመብት ጥሰት፣ ግድያና ውክቢያ፣ የማህበራዊ ፍትህ መጓደል እና ፍትሕ ማጣት፣ የኑሮ ውድነትና ስደት፣ የወያኔ ዱላና አፈና ልክ እንደ ፈርዖን ሰረገሎችና የግብጽ ፈረሶች ከኋላው እያሳደዱት ዛሬ ያለበት አፋፍ ላይ ደርሷል። ከቆመበት አፋፍ ፊት ለፊት ሁለት ነገሮች አሉ። አንደኛው ልክ እንደ ቀይ ባህር የተንጣለለ ገደል ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከባህሩ ማዶ የሚታየው የተስፋ ምድር ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ ካለበት አፋፍ ላይ ቆሞ የሚያልመውና አርቆ ከማዶው የሚያየው ዲሞክራሲ የሰፈነባት፣ እርቅና ሰላም የነገሱባት፣ ሰብአዊ መብቶች የሚከበርባት፣ ፍትሕና ዕርትዕ የተረጋገጡባት፣ ዜጎች በማንነታቸው ሳይዋከቡና ሳይሳደዱ በእኩልነት ተከባብረውና ተከብረው የሚኖሩባት ኢትዮጵያን ነው። እንግዲህ ዶ/ር አብይና የሚሰይሙት ካቢኔ ይህን ገደል ድልድል በመሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ ሊያሻግሩ የሚችሉት፤

  • በአስቸኳይ ሁሉን አቀፍ፣ አሳታፊና ግልጽነት የተሞላው አገራዊ የውይይትና ይምክክር መድረክ ሲፈጥሩ፣
  • ለዚህ ጉዞ መሰናክል የሚሆኑ የሕግ ገደቦችን ሲያስተካክሉ፤ በተለይም የአገሪት ዋና የፖለቲካ ሂደት ተሳታፊ ሊሆኑ የሚችሉ ኃይሎችን ሽብርተኛ አድርገው የሚፈርጁ ሕጎችን፣ የሲቪክ ማህበሩን እና ሚዲያውን የሚጨፈሉ አፋኝ ሕጎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲወገዱና መብትን በሚያሰፉና በሚያከብሩ ድንጋጌዎች እንዲተኩ ሲያደርጉ፤
  • ቀጣዩን ምርጫ መዳረሻ ያደረገ የሽግግር መንግስት የሚቋቋምበትን እና ነጻና ፍትሃዊ ምርጫን ለማካሄድ አመቺ የሆን የፖለቲካ ምህዳር ሲፈጥሩ፤
  • በመላ አገሩት የሚገኙ የፖለቲካ እሥረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ሲያደርጉ እና
  • በሕዝብ ላይ የተጫነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ እንዲነሳ ማድረግ ከቻሉ ነው።

ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ የተጋረጡባቸው ፈተናዎች እና የሚጠብቋቸው ተግዳሮቶች እጅግ ከባድና አስፈሪ ቢመስሉም ከሕዝብ ድጋፍ ጋር ሊወጡዋቸው ይችላሉ ብዮ ተስፋ አደርጋለሁ። መልካሙ ሁሉ እየተመኘሁ ከላይ የተዘረዘሩትን ቁልፍና ወሳኝ እርምጃዎች እውን ለማድረግ እሳቸው ቆርጠው ይነሱ እንጂ የሕዝብ ድጋፍ አይለያቸውም ብዮ አምናለሁ።

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ  5639993994 ወይም 563999-3988 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596  በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *