Hiber Radio: የትንሳዔው ስጦታ – ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እስኪፈቱ ቀሪዎቹን አንርሳቸው!

(በሀብታሙ አሰፋ)

የስቅለት በዓል ሲከበር የአማኙ ዕለቷን ወደ ራሱ መለስ ብሎ ያለፈውን የሚያይበት ፋታ ብዙ ጊዜ የተለያዩ ጥያቄዎች ያጭርብኛል።ደካማ ብጤ ስለሆንኩ ዛሬ ዛሬ ለዚህጭ ቀን እንኳን ለዚያ ሂደት ሳይሞላልኝ ይቀርና በሰበብ አስባብ እርቄያለሁ።ዛሬ በዚህ ቀን ግን ብዙ የሚመላለሱ ሀሳቦች ይጎበኙኝ ይዘዋል። አንዱ ሁሌ ይህን ቀን ባሰብኩ ቁጥር ወደ አእምሮዬ እመጣ ጥያቄ የሚያጭርብኝ ከአለቃ ለማ ቅኔ ውስጥ ደጋግመው ትውስ የሚሉኝ ሁለት ስንኞች ናቸው።

የባለቅኔው መንግስቱ ለማ አባት አለቃ ለማ ከጻፉዋቸው ቅኔያዊ ግጥሞች መካከል ትንሳዔን ባሰብኩ ቁጥር ደጋግሞ ወደ አእምሮዬ የሚመጣው

<<..ስትታመም ታማ ስትሞት ተቀበረች

አንተ ስትነሳ የኔናት የት ቀረች?…>>

የሚለው ቅኔ ነው። በዚያ ቅኔያዊ ግጥማቸው ያብራሩት የአንዲት ሴት ታሪክና የኔን መሰሉ ተራ ሰው ለላይ ላዩ ሀሳብ የሚሰጠው ምላሽን ለማሳየት ሞክረዋል።ሙሉ ስንኞቹን በቃሌ ልወጣው ባለመቻሌ ከታላቅ ይቅርታ ጋር ሀሳቡን በአጭሩ አሰፍራለሁ።  አለቃ ለማ በዚያ ቅኔ ሴቲቱ እናቱዋ የህማማት ዕለት ታማባት ማግስቱን የስቅት ዕለት ሞታለች።የትንሳዔው ዕለት እሱ ሲነሳ የኔናት የት ቀረች ስትል ጥልቅ ሀዘን ላይ ሆና ትጠይቃለች። ያላወቁት ሲታመም ታሞ ሲሞት የማይቀበር ማን አለ ምኒቱ ነሁላላ ሞኛሞኝ ነበረች ሲሉ  እንዳሾፉባት ጽፈዋል።ጥቂቶች የተረዱ ቅኔዋን(ሀሳቡዋን) ሲረዱ ያልተረዳው ሳቀ ይላሉ።

የዶ/ር አብይን የጠ/ሚ/ር ምርጫ ተከትሎ የተፈረመበትን ደብዳቤ የታየ ይመስል ማዕከላዊን ዘጉት፣ኢንተርኔቱን ለቀቁት እና የመሳሰሉት ወሬዎች መናፈስ ጀምረዋል። ለመሆኑ ኢንተርኔቱን ሆነ ሌላ የማዘዝ ሙሉ ስልጣኑን ተረክበው በዚህ በአምስት ቀን ፈጽመውት ከሆነ እሰየው ነው።እሳቸው ለማዘዛቸው እርግጠና ሳንሆን ገና በአቶ ሀይለማሪያም ወንበር በተቀመጡ ማግስት ይህን ተሽቀዳድሞ ማለቱ መቸኮል ይመስላል። ከኢንተርኔቱም በላይ የትግል ጓዳቸው ታዬ ደንደአን ጨምሮ ተዋድቀው ለስልጣን ያበቁዋቸው የኦሮሞ ወጣቶች ዛሬም እተለቀሙ እየታሰሩ ነው።መቼም የበቀደሙን ንግግራቸውን የሰማ ከኢንተርኔቱ በፊት(ትንሽ ደቂቃም ቀደም ብሎ በግፍ የታሰሩትን ሁሉ ይፈታሉ ብሎ ሊያስብ ይችላል።

ጥቂቶች በግፍ አላግባብ ታስረው ተፈተዋል። እነሱ ሲታሰሩም ሆነ ከእነሱ በፊትና በሁዋላ ግን የታሰሩ በሺህ ሚቆጠሩ ዜጎች አሉ። እነዚህ ሲፈቱ ሌሎቹስ የት ቀሩ? በማዕከላዊና ሸዋ ሮቢት የሰው ልጅ ሊያስበው የማይገባው ግፍ የተፈጸመባቸውና ያ አልበቃ ብሎ ከቅሊንጦ ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ታስረው የተሰቃዩና እየተሰቃዩ ያሉ ድረሱልን እያሉ ዛሬም እስር ቤት አሉ። እነ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ አገሬንና ሕዝቤን አገለግላለሁ ብለው የልብ ቀዶ ጥገና ባለሙያነታቸውንና ገንዘባቸውን አፍስሰው ዜጎችን ከሚረዱበት ተይዘው በተቀነባበረ የሀሰት ክስ ታስረው ነጻ ተብለውም አልወቱም።ሌላ ዘዴ ተፈልጎ ፍርዱ ተፈጽሞ ነጻ ሳይወጡ ያልወጡት አሳሪዎቹ ራሳቸው ባነሱት እና ንጹሃንን እገደሉ እሳት የጨመሩበትን የቅሊንጦ ቃጠሎ ለመሸፈን ነው። የዲያስፖራ ቡድንና ልዑካን ከማለት በፊት ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል። ማዕከላዊ የቦታ ለውጥ ስላደረገ ይሄ ሁሉ ጮቤ መርገጥ ምን ይባላል? በስቃይና በመከራ ላሉ ወገኖቻችን ምን ያህል ሕመም የሚፈጥር እኛስ ተረሳን ወይ የሚያሰኝ ነውና ሁሉም የህሊናና ፖለቲካ እስረኞች ከይፋውም ሆነ ከድብቁ እስር ቤት ነጻ እስኪወጡ ድምጻችንን እናሰማ። በዚያ አገር ላይ አንዱ ታሳሪ ሌላው ስልጣኑን ለማስጠበቅ አሳሪ አንዱ በግፍ ሟች ሌላው ገዳይ ሆኖ የሚቀጥልበት ስርዓት እስካልተለወጠ ድረስ ለውጥ የለም።  ስርዓቱ በአንገቱ ላይ ሸምቀቆ የሚያስገባውን ጥቂት የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች የኢትዮጵያ ሕዝብ መከራ አንገፍግፏቸው ያረቀቁትን የህግ ረቂቅ ኤች አር 128 ለማስቀረት ይሁን ለማዘግየትና እስከመጨረሻው ለማስረሳት እየሰራ ነው። በአንድ በኩል በቀጠራቸው ሎቢስቶች በሌላ ጊዜ በጥቃቅን እርምጃዎች ለማዘናጋት ይሞክራል።

በአፍሪካ አንዳንድ አገሮች የቀድሞ ባለስልጣኖች ከሀላፊነት በመፈንቅለ መንግስት ሲነሱ አንድ ሰሞን የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ሁሉ ተመው ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ለዐይን የሚቀፉ ስውርና ግልጽ ማሰቃያዎችን ጉድ እያሉ ጉድ ሲያሰኙ ይከርማሉ፡፡ የአገሬው ሰው ግን በእነ ኢዲ አሚን ዳዳ ሰው እየተበለተ መከራውን ሲያይ ወሬውን ለቀባሪው ማርዳት ነው። ዛሬ የማዕከላዊ ወደ አዲስ የስራ ቦታ መዛወር ያን ያህል ያነጋግራል? ገራፊዎቹ በአዲሱ ቦታ የተለመደ ኢሰብኣዊ የማሰቃያ ተግባራቸውን ከማከናወን የከለከላቸው ባለስልጣን አለ? የሰሞኑ የኤች አር 128 በስርዓቱ ባለስልጣናት ላይ በሰሩት ወንጀልና በፈጸሙት የአገር ሀብት ዝርፊያ ላይ ጫና  የሚፈጥረው የሕግ ረቂቅ መጨረሻው ሲታወቅ የተፈቱት ተመልሰው ላለመታሰራቸው ምን ማረጋገጫ አለ? የለም። እነሱ ከሚሰጡን አጀንዳ ላለመውጣት ሰበብ መፍጠር ብቻ።

ሀይማኖተኞቹ ስለ ፍቅር ስለ ዓለም የተሰቀለውን ክርስቶስ ሲማልዱ ያለ ሀጢያታቸው በግፍ የታሰሩትን የዋልድባ መነኮሳቱን ጨምሮ በሺህ ስለሚቆጠሩት በስውርና በግልጽ እስር ቤት ያሰቃዩ ግፈኞችን ስለማያወግዙት ይልቁኑ ሙዳይ ምጽዋት አራግፈው የቤተ ክርስቲያኑዋን ሀብት ባንክ እያቋቋሙ ገንዘብ ማሸሽ ስሌአዙት የወያኔው አባት አባ ማቲያስ እና  ግብረ አበሮቻቸው አውግዘዋል? በእውኑ የሚያሳስበን የሚያበሳጨን ዓመት ቆጥረን የምናስታውሰው ሺህ ዓመታትን ያሳለፈውን  የእነ ቀያፋ እና ጲላጦስ ተግባር የእነ ይሁዳ ክዳትና መጨረሻ ታሪክና የክርስቶስን መከራ ብቻ ነው ወይስ እሱ ራሱ እንዳለው ለወንድሙ ያደረገ ለኔ አደረገ ነውና በእሱ አምሳል የተፈጠሩ ወገኖቻችን መከራና ስቃይ እንዴት አያስቆጨንም ? የታሉ የሀይማኖት አባቶች ጩኸት ?ከጥቂቶች በስተቀር የብዙዎቹ ድምጽ አይሰማም። እነደ አቡነ ማቲያስ ያሉ  ከገዳዮቻችን ጋር ያበሩትን ግን ስማቸውን ስንጠራና ስንዘክር እንውላለን።

ዛሬም በግፍ እስር ላይ ያሉ እውቁ የነጻነት ታጋይ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨመምሮ፣እነ መ/አ ማስረሻ ሰጤ፣እነ ታዬ ደንደአ እነ ስዩም ተሾመ ፣እነ ለገሰ ወልደሃና እና እነ እከሌ በስም ቆጥረንና ጠርተን የማናውቃቸው ከተኙበት፣ከስራ ቦታ፣ ከመንገድ እየታፈኑ የታሰሩ የግፍ እስረኞች በሙሉ የሚፈጸምባቸው ስቃይ ቆሞ ከእስር እንዲፈቱ ድምጻችንን እናሰማ።

መልካም የትንሳዔ በዓል

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 6፤30 ሰዓት እስከ 8  ሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ  5639993994 ወይም 563999-3988 ፣ 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596  በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው ። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *