Hiber Radio: ዶክተር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ የ62 ተካሳሾች ክስ እንዲነሳ ተወሰነ፣አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ የቀሩ እስረኞችም እንዲፈቱ ጥያቄው ቀጥሏል

በይድነቃቸው ከበደ

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶክተር ፍቅሬ ማሩን ጨምሮ የ62 ተከሳሾችን የክስ ሂደት ማንሳቱን አስታወቀ።

ተከሳሾቹ የወንጀለኛ መቅጫ ህግን አንቀጽ 464 እና 494 በመተላለፍ ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ያለና እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠባቸው ናቸው።

የመንግስቱ ዜና አገልግሎት ኢዜአ ከፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባገኘው መረጃ መሰረት በእነ አበበ የኋላ መዝገብ የተጠቀሰውን አንቀጽ በመተላለፍ ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ያለ 18 ተከሳሾች ክስ እንዲነሳ ተወስኗል።

በእነ ማስረሻ ሰጠኝ መዝገብ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ምድብ ችሎት ጉዳያቸው ሲታይ ከነበሩት 38 ተከሳሾች መካከል አራቱ በሰው መግደል ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠ ሲሆን፤ ስምንቱ ደግሞ በነጻ መሰናበታቸው ይታወቃል።

በተጠቀሰው መዝገብ የወንጀለኛ ህጉን አንቀጽ 464 እና 494 በመተላለፍ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠባቸውን ቀሪ 26 ተከሳሾች ክስ እንዲነሳ ሲወሰን፤ በሰው መግደል ወንጀል እንዲከላከሉ የተበየነባቸው የአራቱ ተከሳሾች የፍርድ ሂደት ግን ባለበት ይቀጥላል ተብሏል።

በተመሳሳይ በእነ ቴዎድሮስ ዳንኤል መዝገብ የወንጀለኛ ህጉን አንቀጽ 464 እና 494 በመተላለፍ ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ያለ የ18 ተከሳሾች ክስ እንዲነሳ መወሰኑን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታውቋል ሲል ጽፏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአንድ ሳምንት በላይ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ የተደረገለት የዕውቁ ነጻነት ታጋይ አንዳርጋቸው ጽጌና ቀሩትም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ እየተጠበቀ ሲሆን ጥያቄውም ቀጥሏል።

በቃሊቲ ብቻ በኦነግ ስም የታሰሩ ከኬኒያ ታፍኖ የመጣውን መስፍን ጨምሮ ቢያንስ በስም የሚታወቁ 49 እስረኞች እንዳሉ መጠቀሱ ይታወሳል።በግንቦት ሰባት ስም የታሰሩ ከእስር ቤት ታፍነው ወደ አልታወቀ ቦታ 77 የአማራ ብሄር ተወላጅ እስረኞች መወሰዳቸውን ለገሰ ወ/ሃና ዛሬ መጻፉ ይታወሳል።

ዶ/ር አብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት በኬኒያና በሱዳን ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ባቀረቡት ጥያቄ ኢትዮጵያውያን እስረኞች ይፈታሉ መባሉን ተከትሎ ሰሞኑን በአገር ቤት ያሉትም እንዱፈቱ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብ መቆየቱ ይታወሳል። ከትላንት ጀምሮ የዶ/ር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ የ62 የፖለቲካ እስረኞችን ክስ መቋረጥ የዘገበው የአገዛዙ ዜና አገልግሎት   ከሱዳን 1400 እና ከኬንያ 1600 እስረኞች ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሀገራቱ መሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት መፈታታቸው ዘግቧል።

ሕብር ሬዲዮ ባለፈው እሁድ በሱዳን ያሉ ስደተኞችን ጠቅሰን የዶ/ር አብይን ጉዞ ተከትሎ ቃል በተገባው መሰረት ከሱዳን እስረኞች ያለመፈታታቸው የተዘገበ ሲሆን ከዘገባው በሁዋላ ረቡዕ ተፈተዋል ሲል የመንግስቱ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ  5639993994 ወይም 563999-3988 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596  በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *