Hiber Radio: ለሀገር ሰላም፣ ለሕዝብ ደህንነት ሲባል የህወሓት አመራሮች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው!

በስዩም ተሾመ

“‘ፍቅር እንዲማሩ’ ብለን የእስር ማዘዣ ካወጡብን ሰዎች ጋር አብረን ማዕድ እየተቋደስን ነው!” ይህ ዶ/ር አብይ ጠ/ሚኒስትር ሆነው የተመረጡ ሰሞን ለታዋቂ የኦሮሞ ተወላጆች በቤተ-መንግስት ባዘጋጁት የእራት ግብዣ ላይ የተናገሩት ነው። የእስር ማዘዣ የወጣባቸው እሳቸውን ጨምሮ አምስት የኦህዴድ ባለስልጣናት እንደሆኑ ተገልጿል። በእርግጥ እኔ ከአንድ ወር በፊት ህወሓቶች ከፍተኛ የኦህዴድንና ብአዴን አመራሮችን እስር ቤት ለማስገባት አቅደው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ገልጬ ነበር። ዶ/ር አብይ ተናገሩ ከተባለ በኋላም የኦህዴድና ብአዴን አመራሮችን ጠይቄ ለማረጋገጥ እንደቻልኩት በእርግጥ የእስር ማዘዣው ተቆርጦ ነበር።

“በእነ ጌታቸው አሰፋ የሚመራው ቡድን ዶ/ር አብይ እና ለማ መገርሳን ጨምሮ በአምስት የኦህዴድ አመራሮች ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቶ ነበር” የሚለው ለብዙዎች አይዋጥላቸውም። ይህ ደግሞ ከሁለት ዓይነት እሳቤ የመነጨ ነው። አንደኛ፡- እንደ ለማ መገርሳና ዶ/ር አብይ ያሉ መሪዎችን ማሰር ከኦሮሚያ አልፎ መላ ሀገሪቱን ምን ዓይነት ቀውስ ውስጥ ሊከታት እንደሚችል በራሳቸው በማሰብ “ሕሊና ያለው ሰው ይህን አያደርግም” የሚል ነው። ሁለተኛ፡- ዶ/ር አብይ “‘ፍቅር የማራሉ’ ብለን የእስር ማዘዣ ካወጡብን ሰዎች ጋር አብረን ማዕድ እየተቋደስን ነው!” የሚለው የዶ/ር አብይ አባባል “ግራህን ሲመታህ ቀኝህን አዙርለት” የሚሉት ዓይነት ነው። ስለዚህ ዶ/ር አብይ የፖለቲካ እንጂ መንፈሳዊ መሪ አይደለም። “ፍቅርን እንዲማሩ ብዬ እስር ቤት ሊያስገቡኝ ከነበሩ ሰዎች ጋር ማዕድ እየተቋደስኩ ነው” ብሎ ሲናገር ማመን ከባድ ነው።

ይሁን እንጂ፣ እነ ዶ/ር አብይ ቢታሰሩ ኖሮ በሀገሪቱ ውስጥ ሊከሰት ይችል የነበረው ሁከትና ብጥብጥ ሆነ የዶ/ር አብይ መንፈሳዊ የሚመስል ፍቅርና ይቅርታ በህወሓቶች ዘንድ ቅንጣት ያህል ዋጋና ትሩጉም አልተሰጠውም፥ አይሰጠውም። በዜጎች ላይ የሚደርሰው ግፍና በደል፣ በሀገር ላይ የሚያስከትለው ጉዳትና ኪሳራ ወይም ከዶ/ር አብይ ያገኙት ፍቅርና ይቅርታ፣ … ወዘተ በህወሓቶች ዘንድ አሳሳቢ አይደለም። ምክንያቱም የህወሓቶች መነሻና መድረሻ የራሳቸውን የበላይነትና ተጠቃሚነት ማስቀጠል ነው። ለእነሱ የፖለቲካ ትርጉምና ፋይዳ የስልጣን የበላይነትና ተጠቃሚነት ብቻ ነው።

የህወሓትን የስልጣን እና የኢኮኖሚ ብዝበዛ ለማስቀጠል በምድር ላይ ያለ ነገር ሁሉ መስዕዋት ይደረጋል። ለምሳሌ የሀገር ሉዓላዊነትና ነፃነት በስልጣንና ቁሳዊ ሃብት ሊለወጥ ይችላል፣ በስልጣን ላይ ለመቆየት ዜጎችን በተናጠል ከመግደልና ማቁሰል አልፎ በጅምላ-ጨራሽ መሳሪያ እስከመጨፍጨፍ ሊደርስ ይችላል። እንኳን ለሚወክሉት የፖለቲካ ማህብረሰብ ወልዶ-ላሳደጋቸው ቤተሰብ ፍቅር የላቸውም፣ ለባላንጣ ይቅርና ለዕድሜ-ልክ ወዳጅ ምህረት አያደርጉም። ምክንያቱም ከራስ-ወዳድነት የተረፈ እንጥፍጣፊ ፍቅር በውስጣቸው አይገኝም። በተለይ የህወሓት መስራቾችና አንጋፋ አመራሮች ከባርነትና ጭቆና በስተቀር ስለ ሕዝብ ነፃነትና እኩልነት ምንም ነገር አያውቁም።

የትኛውም የፖለቲካ ቡድን ለህወሓቶች መገልገያና መጠቀሚያ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የለውም። ለዚህ ደግሞ በትጥቅ ትግል ወቅት ትግራይ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የነበራቸውን ግንኙነት መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ ኢዲዩና ኢህአፓ ድርግን ከስልጣን ለማስወገድ የሚታገሉ ድርጅቶች ሲሆን ከትግራይ ክልል ለቅቀው የወጡት በደርግ ሳይሆን ህወሓት በከፈተባቸው ጦርነት ነው። ከዚህ በተጨማሪመ አሁን በስም የማላስታውሰውና በምስራቃዊ የትግራይ አከባቢዎች ሲንቀሳቀስ የነበረ የፖለቲካ ቡድን አመራሮችና አባላት ከህወሓት ጋር ለመደራደር መጥተው ሳለ ሌሊት በተኙበት በጥይት መረሸናቸውን እንደ እያሱ መንገሻና አረጋዊ በርሄ ያሉ የቀድሞ የህወሓት አመራሮች በመፅሃፎቻቸው ገልፀዋል።

 

ህወሓት ኢህአዴግን ሲመሰርት የተቀሩትን ሦስት አባል ድርጅቶች ያቋቋማቸው የህወሓት መገልገያና መጠቀሚያ እንዲሆኑ በማሰብ ነው። ህወሓት ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የሚለውን ድርጅታዊ አሰራር ያመጣው የተቀሩት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የተለየ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት እንዳይዙ ለማድረግ ነው። ከዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ልጓምን ለመበጠስ ጥረት ያደረገ የኢህአዴግ አባል ድርጅት ወይም መሪ አይቀጡ-ቅጣት ተቀጥቶ መጨረሻው ውርደት፥ ስደት፥ እስራት… ወዘተ ይሆናል። ከኢህአዴግ ውጪ ያሉ “ተቃዋሚ” የፖለቲካ ድርጅቶችም የህወሓት መገልገያ ካልሆኑ እድሜያቸው አጭር ነው። ምክንያቱም ከህወሓት የተለየ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ያለው ድርጅት በሸርና አሻጥር ወዲያው ይፈርሳል። ለዚህ ደግሞ ኦነግ፥ ቅንጅት፥ አንድነት፥… እያሉ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

ለህወሓት የፖለቲካ ቡድኖችና ድርጅቶች ቀርቶ የራሱ አባላትና አመራሮች እንኳን ከመገልገያነትና መጠቀሚያነት የዘለለ ፋይዳ የላቸውም። ማንኛውም አባልና አመራር ህወሓት ውስጥ መቆየት የሚችለው ከድርጅቱ መስራቾችና አመራሮች የተለየ አቋምና አመለካከት እስካልያዘ ድረስ ብቻ ነው። ህወሓት ውስጥ የተለየ ሃሳብና አስተያየት ያላቸው አመራሮች መጨረሻቸው ምን እንደሆነ ከእነ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) እስከ እነ ስዬ አብርሃ ያሉትን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። እንደ ኦህዴድ ካሉ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አመራሮች ደግሞ ከእነ ዮናታን ዲቢሳ እና አልማዝ መኮ እስከ ጁነዲን ሳዶ ያሉትን መጥቀስ ይቻላል።

በሀገርና ሕዝብ ጉዳይ ላይም ቢሆን የህወሓቶች አቋም ወጥና ተመሳሳይ ነው። በህወሓቶች ዘንድ “ሀገር” ማለት ከመጠቀሚያነት የዘለለ ፋይዳ የለውም። ለዚህ ደግሞ ከአሰብ ወደብ እስከ ባድመ ድረስ ህወሓቶች የፈፀሙትን ክህደት መጥቀስ ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ህዝብም ቢሆን በህወሓቶች ዘንድ ከስልጣን መወጣጫነትና የሃብት ምንጭነት የዘለለ ፋይዳ የለውም። በፖለቲካው ላይ ያላቸው የስልጣን የበላይነት አደጋ ላይ የወደቀ መስሎ በተሰማቸው ቁጥር የሀገሪቱን ህዝብ በጥይት ያጭዱታል፣ በእስር ቤት ያጉሩታል፣ ከመኖሪያ ቤቱና መሬቱ ያፈናቅሉታል።

ከሌላው በተለየ ደግሞ የትግራይ ሕዝብን የስልጣን መወጣጫ ሆኖ እንዲያገለግላቸው በጥብቅ ይከታተሉታል፥ ይቆጣጠሩታል። ለዚህ የሚሆን ከክልል ጀምሮ እስከ ሰፈርና ጎጥ የሚደርስ የቁጥጥርና ክትትል አደረጃጀት ዘርግተዋል። የትግራይ ህዝብ ለህወሓት የስልጣን መወጣጫ መሆኑ ያበቃ እለት ግን ከተቀረው የኢትዮጲያ እና የጎረቤት ሀገሮች ጋር ደም-አፋሳሽ ግጭትና ዕልቂት ውስጥ እንደሚከቱት አልጠራጠርም። ለዚህ ደግሞ በዙሪያው ካለው የአማራ ሕዝብ ነጥለውታል፣ ከኤርትራ ሕዝብ አቃቅረውታል፣ ከአፋር ሕዝብ ጋር ደግሞ ቂምና በቀል ደግሰውለታል።

ዶ/ር አብይ “‘ፍቅር እንዲማሩ’ ብለን የእስር ማዘዣ ካወጡብን ሰዎች ጋር አብረን ማዕድ እየተቋደስን ነው!” በማለት ፍቅርና ይቅርታ የሚያሳየው ለእነዚህ የህወሓት አመራሮች ነው። ከደርግ የተረከቧትን ሀገር እየከፋፈሉ ለባዕዳን የሸጡ ሰዎች ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ ለምንና እዴት ሊያስቡ ይችላሉ? ወልዶ ላሳደጋቸው የትግራይ ሕዝብ ፍቅርና አክብሮት ያነሳቸው ሰዎች ለተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሆን ክብርና ፍቅር ከየት ያመጡታል? ለእነ አረጋዊ በርሄ፣ ስዬ አብረሃ፣ ገብሩ አስራት፣ … ከመሳሰሉ የትግል ጓዶቻቸው ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት በውይይትና ይቅርታ ማለፍ የተሳናቸው ሰዎች የዶ/ር አብይን ይቅርታ እንዴት ሊገነዘቡት ይችላሉ። ዘወትር ስለራሳቸው ስልጣንና ጥቅም የሚያስቡ ሰዎች እንዴት ሀገርና ሕዝብ ሕልውና ላይ እንዲወስኑ ዕድል ይሰጣቸዋል?

በአጠቃላይ የህወሓት መስራቾችና አመራሮች እስካሁን በሀገርና ሕዝብ ላይ የፈፀሙት ይበቃል። ከዚህ በኋላ ግን የእነሱ ግፍና በደል ሊያበቃ ይገባል። ለሀገርና ሕዝብ ፍቅር የሌላቸው ሰዎች ይቅርታና ምህረት አይገባቸውም። እስካሁን የፈፀሙት ግፍና በደል መቋጫ የሚያገኘው ለፍርድ ቀርበው ሲዳኙ ብቻ ነው። ስለዚህ በሀገር ላይ ክህደት፣ በህዝብ ላይ በደል የፈጸሙ የህወሓት መስራቾችና አመራሮች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው!!

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ  5639993994 ወይም 563999-3988 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596  በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *