Hiber Radio እነ ዘመነ በእስር ቤት የተፈጸመባቸውን ድብደባ ፍርድ ቤት እንዳይናገሩ ተከላከለ ፣<<ጺሜን በእሳት አቃጥለውኛል!>> ተከሳሽ <<ዝም በል ችሎት እየደፈርክ ነው!>> ፍርድ ቤት

mead

(ህብር ሬዲዮ-ላስ ቬጋስ) የመኢአድ ም/ፕሬዝዳንት አቶ ዘመነ ምህረትን ጨምሮ ዛሬ ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ነኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ዐቃቤ ሕግ በሽብር የከሰሳቸው የተቃዋሚ አባላት የሆኑትተከሳሾች በእስር ቤት የደረሰባቸውን ስቃይ እንዲናገሩ ለማይፈቅድ፣ሕክምና ተከልክለው እያለ ይህንን የማያደምጥ በትዕዛዝ ፍርድ ለሚሰጥ ፍርድ ቤት ጠበቃ ማቆም አንፈልግም በማለታቸው ከተከሳሾቹ አንዱ <<በሽብር ወንጀል የተከሰሰ ህክምና አይፈቀድለትም ተብያለሁ፣ ጺሜን በእሳት አቃጥለውኛል >> ብሎ በሚናገርበት ወቅት የችሎቱ ዳኞች በተደጋጋሚ በተጽዕኖ እንዲያቋርጥና ሁሉም በደላቸውን ለመናገር የሞከሩትን በችሎት መድፈር እንደሚጠየቁ ዛሬ ሰኔ 11 ቀን 2007 በዋለው ችሎት ገልጸዋል።

የዛሬውን የፍርድ ቤት ውሎ የተከታተለው የመኢአድ የቀድሞ ም/የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ለገሰ ወ/ሃና እንደገለጸው የመኢአድ ም/ር ፕሬዝዳንት አቶ ዘመነ ምህረት ፣ ሌላው የፓርቲው አባል መለሰ መንገሻና ጌትነት ደርሶ በተከሰሱበት የሽብር ወንጀል በዛሬው ቀጠሮ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት በእነ ዘመነ መዝገብ ሶስቱም መቅረባቸውን ፍርድ ቤቱ ካረጋገጠ በሁዋላ<< በግል ጠበቃ አቆማለሁ ያለ ከእናንተ ውስጥ ማነው?>> ሲል የግራ ዳኛው ሲጠይቅ አቶ ጌትነት ደርሶ <<እኔ ጠበቃ አልፈልግም ነው ያልኩት በትዕዛዝ ፍርድ የሚሰጥ ፍርድ ቤት ምን አገኛለሁ ብ ጠበቃ አቆማለሁ አላደርገውም የደረሰብኝን በደል መስማት የማይፈልግ ፍርድ ቤት 2ወር ከ14 ቀን በጨለማ ክፍል መሰቃየቴን እንዳልናገር የሚከለክል ፍርድ ቤት ምን ሊጠቅመኝ ጠበቃ አቆማለሁ በአካሌ ላይ የደረሰውን ጉዳት ለችሎት እንዳላሳይ የሚከለክል ፍርድ ቤት ጠበቃ አያስፈልግም በደረሰብኝ ድብደባ ጆሮየ አይሰማም ብዙ ቦታ ተጎድቻለሁ ህክምና ብጠይቅ የክሴን ሁኔታ አይተው በሽብር የተከሰሰ ህክምና አያገኝም ተብየ ይህንን በደል መስማት የማይፈልግ ፍርድ ቤት >> ብሎ ንግግሩን ሳይጨርስ ዳኛው አቁም በማለት ንግግሩን አቋርጠውታል።

በዚሁ የዛሬው ችሎት ላይ አቶ ዘመነ በበኩሉ ለፍርድ ቤቱ እንደተናገረው <<ጌትነት በድብደባ ብዛት ጆሮው አይሰማም ጮክ ብላችሁ ንገሩት እኛ አማራ በመሆናችን ብቻ እራቁታችንን ተደብድበናል አሁን ባለሁበት ቅሊንጦ የአጋአዚ አባል አንተን እንገድልሀለን እያለ ይዝትብኛል ለህይወቴ እሰጋለሁ >> ብሎ ንግግሩን ሳይጨርስ ዳኛው በቁጣ ለማቋረጥ ቢሞክርም ዘመነ ንግግሩን ቀጥሎ << ይህንን ለዚህ ፍርድ ቤት መናገር እከለከላለሁ ህይወቴ አደጋ ላይ ነው ለማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ ይሰጥልን >> በማለቱ ዳኛው በድጋሚ በቁጣ በተደጋጋሚ ችሎት እንደሚደፍሩ በዚህም አንድ ዓመት ድረስ ሊቀጡ እንደሚችሉ የገለጸ ሲሆን ማስፈራሪያውን ወደ ጎን በማድረግ አቶ ዘመነ አስቀድሞ አቶ ጌትነት የተናገረውን አጠናክሮ መናገር ሲቀጥል ዳኛው በጩኸት ያስቆመው ሲሆን ፖሊሶችም ተጠግተው አፉን በመቆም በጫና አቤቱታው መቋረጡን ይሄው መረጃ ያሳያል።

ሌላው ተከሳሽ አቶ መለሰ መንገሻ የዘመነን ንግግር ያቃረጠውን ችሎት ጠይቆ ምላሽ ሳይጠብቅ ንግግሩን የቀጠለ ሲሆን <<ከመቶ ዓመታት በፊት የነበሩ የኢትዮጵያ ነገስታት ስም እየተጠራ ያድኑህ >> ብሎ ንግግሩን ሳይጨርስ ዳኛው በቁጣ ለማቋረጥ ቢሞክርም መለሰ መናገሩን ቀጥሎ << ፂሜን በእሳት አቃጥለውኛል እራቁቴን ተደብድቤለሁ>> ብሎ ለሁለተኛ ጊዜ ሶስቱም ዳኞች ጮኸው ንግግሩን ማስቆማቸውን ችሎቱን የተከታተሉት የላኩት ይሄው መረጃ ይገልጻል። ተከሳሾቹ የደረሰባቸውን በደል እንዳይናገሩ ሲከላከሉ ከቆዩት ዳኞች አንዱ በድጋሚ ችሎት በመድፈር እስከ አንድ እንፈርዳለን የሚል ዛቻ ያሰማ ሲሆን ቀጣዩን ቀጠሮ ለሐምሌ 16 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ተከሳሾቹ ግንቦት 27 ቀን 2007 በዚሁ ችሎት በቀረቡበት ወቅት ለፍርድ ቤቱ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የደረሰባቸውን ስቃይ የገለጹ ሲሆን በዚህም ራቁታቸውን ትግርኛ ተናገሩ እየተባሉ በአማራነታቸው መደብደባቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የመኢአድ ሕጋዊው ፐ/ት አቶ ማሙሸት አማረ በአራዳ ምድብ በዝግ በታ ችሎት ፍርድ ቤቱ በአምስት ሺህ ብር ዋስ እንዲፈቱ ቢወስንም የዋስትናው ተከፍሎ ካለቀ በሁዋላ ፖሊስ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሰረት እንዳልፈታቸው ከአዲሲ አበባ የፍርድ ቤቱን ውሎ ተከታትለው መረጃውን የላኩልን አረጋግጠዋል። አቶ ማሙሸት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይፈቱ ሲቀር ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ቤተሰብ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሰረት አምስት ሺህ ብር የዋስትና ገንዘቡን የከፈለ ሲሆን እስካሁን አልተፈቱም።

የፓርቲው የቀድሞ ም/የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ለገሰ ወ/ሃና ዛሬ ሰኔ 10 ቀን 2007 በጊዜ ቀጠሮ ሚመላለሱበት አራዳ ምድብ ችሎት ጉዳያቸውን በዝግ ተመልክቶ አቶ ማሙሸት አማረ በአምስት ሺህ ብር ዋስ ወጥተው በቀጣዩ ቀጠሮ ሐምሌ 2 ቀን 2007 እንዲቀርቡ የወሰነ ቢሆንም ፖሊስ ለሁለተኛ ጊዜ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ወደ ጎን ትቶ አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

Court_order_mamushet_3

 

ግንቦት 5 ቀን 2007 ከቤታቸው አቅራቢያ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ በተለምዶ ቴዲ ባር አጠገብ በደህንነቶች ታፍነው የታሰሩት የመኢአድ ሕጋዊው ፕ/ት አቶ ማሙሸት አማረ ሲኤም ሲ በሚገኘው ቦሌ ምድብ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ግንቦት 25 ቀን 2007 ክሱ ተቋርጦ ከእስር እንዲፈታ ሲሉ ጉዳዩን ሲያዩ የቆዩት ዳኛ ብርቱካን ገላው እንዲለቀቅ ትዕዛዝ ቢሰጡም ውሳኔው ተግባራዊ ሳይሆን ከዚያው ፍርድ ቤት ከቦሌ ፖሊስ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ እስር ቤት በተለምዶ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ በሚባለው ማዕከላው አጠገብ ወደሚገኘው እስር ቤት ተዛውረው በአዲስ ክስ የጊዜ ቀጠሮ እንደ አዲስ ተጠይቆባቸው ነበር። አቶ ማሙሸትን ፖሊስ ለሁለተኛ ጊዜ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ አልፈታም ማለቱን አስቀድመን መዘገባችን ይታወሳል።

ህብርን ከድህረ ገጻችንና ከዘ-ሐበሻ ድህረ ገጽ በተጨማሪ በቀጥታ በስልክ በማንኛውም ጊዜ 712 -432-8451 በመደወል ብቻ ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *