Hiber Radio የፕ/ት ኦባማ የኢትዮጵያውን አገዛዝ ምርጫ መቀበል ተቃውሞ አስነሳ ፣የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኦባማ በሚገኙበት የቤተ መንግስቱ የራት ግብዣ አልገኝም አሉ

ፕ/ት ኦባማ በኢትዮጵያ መግለጫ ሲሰጡ፣ ኢ/ር ይልቃል
ፕ/ት ኦባማ በኢትዮጵያ መግለጫ ሲሰጡ፣ ኢ/ር ይልቃል
  • ‹‹ኦባማ ኢህአዴግን በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጠ ነው ማለታቸው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ግንባታ ላይ ውሃ የሚቸልስ ነው››

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት የኢትዮጵያ መንግስት ዛሬ ሀምሌ 20/2007 ዓ.ም ምሽት 1፡00 ሰዓት ላይ ቤተ መንግስት ውስጥ ለአሜሪካው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ የሚያደረገው የእራት ግብዣ ላይ እንደማይገኙ መግለጻቸውን ነገረ ኢትየጵያ ዘገበ፡፡ የራት ግብዣው ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጥሪ የተደረገላቸው ኢ/ር ይልቃል ‹‹ አሸባሪ አድርጎ የሚቆጥረን ኢህአዴግ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ሲመጡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ለማስመሰልና ዕውቅና ለማግኘት ያደረገው በመሆኑ አልገኝም›› ብለዋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል አክለውም ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ ጭቆና እና ስቃይ ውስጥ ባለበት በአሁኑ ወቅት ኢህአዴግ የጠራው የቅንጦት ግብዣ ላይ መገኘት የህዝቡን ሰቆቃ እንደመርሳት እቆጥረዋለሁ›› ማለታቸውን ጠቅሷል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ መግለጫ በሚሰጡበት ወቅት ኢህአዴግ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ነው ማለታቸው ቅር እንዳሰኛቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኢህአዴግን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ነው ማለት የሰላማዊ ታጋዮችን ስቃይ የሚክድና ለአምባገነኖች ይሁንታ የሚሰጥ ነው›› ሲሉ የፕሬዝደንት ኦባማን ንግግር ነቅፈውታል፡፡ ፕሬዝደንት ኦባማ የጠበንጃ ትግልን አለመደገፍን ለመግለፅ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንትን ጨምሮ ሌሎች የአሜሪካ ተቋማት ኢ-ዴሞክራሲያዊ መሆኑን አረጋግጠውት፣ መቶ ፐርሰንት ምርጫ አሸንፌያለሁ የሚልን ፓርቲ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንደተመረጠ መግለፃቸው እንዳሳዘናቸው ኢ/ር ይልቃል ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ኢ/ር ይልቃል በነገው ዕለት የአሜሪካ ኤምባሲና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በጋራ ያዘጋጁት ስብሰባ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕ/ት ኦባማ በኬኒያ ቆይታቸው በዲሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ፣በመገናኛ ብዘሁሃን ነጻነት አንጻራዊ በሆነ መንገድ ከኢትዮጵአ በተሻለችው ኬኒያ አገርን በዘር ከፍሎ ማስተዳደር ጉዳት እንዳለው፣ልዩነትን ማጥበብ እንደሚያስፈልግ በይፋ የገለጹ ሲሆን በዘር ላይ የተመሰረት ስርዓት ባቆመው የኢትዮጵያው አገዛዝ ላይ ተመሳሳይ ንግግር አለማድረጋቸው ቅሬታ አስነስቷል። በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ መቶ በመቶ ያሸነፈበትና የራሳቸው መንግስት ያልተቀበለውን ምርጫ ኦባማ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ማለታቸው ከሰማአዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ብቻ ሳይሆን በበርካታ ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ ሚዲያው ተቃውሞ አስከትሏል። ዶ/ር መራራ ጉዲና ከዚህ ቀደም የኦባማ ጉዞን አስመልክቶ ለህብር ሬዲዮ በሰጡት ቃለ መጠይቅ የኦባማ ጋና ላይ የተናገሩትን ረስተው ከአምባገነኖች ጋር መሞዳሞድ እሳቸውን የዲሞክራሲ ትግል ምሳሌ አድርገው ለሚቆጥሩ ለአፍሪካ በአጠቃላይ ለዓለም ወጣቶች አሳዛን ለራሳቸውም አሳፋሪ እርምጃ መሆኑን መግለጻቸው አይዘነጋም።

<<ኦባማ በግልጽ ከአምባገነኖች ጋር መሞዳሞዳቸው የራሳቸውን ታሪክ የሚያበላሽና እሳቸውን የዲሞክራሲ ትግል ተምሳሌት ማድረግ እንደማይቻል አሳይተዋል>> የሚሉ የሰላ ተቃውሞዎች በማህበራዊ ሚዲያው ንግግራቸውን ተከትሎ በኢትዮጵያውያን መቅረብ ጀምረዋል።

ህብር ሬዲዮን በየቀኑ በድህረ ገጻችን ወይም በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *