አይ.ሲ.ስን ለመቃወም አደባባይ የወጡ ዛሬም ከእስር ቤት ፍርድ ቤት እየተጉላሉ ነው

semayawi_meyad_prisoners_01

  • የመኢአድ ፕ/ት አቶ ማሙሸት አማረ ለነሃሴ 20 ተቀጥሮበታል

አይ ኤስ አይ ኤስ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ ለመቃወም መንግስት በጠራው ሰልፍ ሰበብ የታሰሩት እነ ማቲያስ መኩሪያ ለነሃሴ 18/2007 ዓ.ም እንደተቀጠረባቸው ነገረ ኢትዮጵአ ዘገበ፡፡ ፖሊስ በጊዜ ቀጠሮ ወቅት ‹‹የቪዲዮ ማስረጃም አለን›› በማለቱ ተከሳሾቹ ‹‹ቪዲዮው ይቅረብልን፡፡ የቪዲዮ ማስረጃው ለእኛም የመከላከያ ምስክርነት ይጠቅመናል›› ብለው ጠይቀው የነበር በመሆኑ፤ ፍርድ ቤቱ የቪዲዮ ማስረጃው መቅረብ እንዳለበትና እንደሌለበት ብይን ለመስጠጥ ለዛሬ ነሃሴ 5/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡ ይሁንና የመናገሻ ፍርድ ቤት በዛሬው ዕለት የማይሰራ በመሆኑ ችሎቱ በአራዳ ፍርድ ቤት በተረኛ ዳኛ ታይቷል፡፡ የልደታ ፍርድ ቤትም ‹‹ጉዳዩ አልተመረመረም፡፡›› በሚል ብይን ለመስጠት ለነሃሴ 18/2007 ዓ. ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ቪዲዮው ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሲሰጥ የዛሬው ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን ተከሳሾቹም እየተጉላሉ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ ማቲያስ መኩሪያ ‹‹በቪዲዮው ጉዳይ ለመወሰን ለሶስተኛ ጊዜ ሲቀጠር ነው፡፡ እኛም ቤተሰቦቻችንም እየተጉላላን ነው፡፡›› ሲል ቅሬታውን አቅርቧል፡፡ በተመሳሳይ 2ኛ ተከሳሽ መሳይ ደጉሰው ‹‹ድሃ ቤተሰብ አለን፡፡ ቤተሰቦቻችን መርዳት እንዳንችል እየተጉላላን ነው፡፡›› ብሏል፡፡ በማቲያስ መኩሪያ መዝገብ የተከሰሱት 1ኛ ማቲያስ መኩሪያ፣ 2ኛ መሳይ ደጉሰው፣ 3ኛ ብሌን መስፍን፣ 4ኛ ተዋቸው ዳምጤ ሲሆኑ ከመሳይ ደጉሰው ውጭ ያሉት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ በተመሳሳይ በአራዳ ፍርድ ቤት የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው አቶ ማሙሸት አማረም ለነሃሴ 20/2007 ዓ.ም ተቀጥሮበታል፡፡ አቶ ማሙሸት የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ‹‹ምስክሮቹ ስላልተሟሉና ብዙ መዝገቦችም ስላሉ ምስክርነት መስማት አልቻልንም›› በሚል ምስክሮቹ ሳይሰሙ ቀርተዋል፡፡ በተጨማሪም የአንድነት አባልና የሚሊዮኖች ድምፅ ጋዜጣ አምደኛ የነበረው እስማኤል ዳውድ አራዳ ፍርድ ቤት ቀርቦ ለነሃሴ 28/2007 ዓ.ም ተቀጥሮበታል፡፡ ፍርድ ቤቱ ‹‹በክረምት ከማይሰሩ የተለያዩ ፍርድ ቤቶች መዝገቦች በመምጣታቸው ምስክር መስማት አልቻልንም፡፡ ስራ በዝቶብናል›› በሚል በበርካታ ተከሳሾች ላይ ረዘም ያለ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን በተለይ በሰልፉ ሰበብ የታሰሩ ተከሳሾች በተለይም ሴቶች እና ቤተሰቦቻቸው የተፋጠነ ፍርድ ልናገኝ አልቻልንም በሚል ፍርድ ቤቱ ግቢ ውስጥ ሲያለቅሱ ተስተውለዋል ሲል ይሄው ነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ ያስረዳል።ይህ በእንዲህ እንዳለ በስልታን ላይ ያለው አገዛዝ አይ.ሲስን ለመቃው አደባባይ ከወቱት መካከል ተቃዋሚ አላቸውን አፍሶ.አንዳንዶቹም በሰልፉ ባይገኙም ተቃዋሚ በመሆናቸው ብቻ በሀሰት ክስ ተለጥፎባቸው በእስር እየማቀቁ ሲሆን አይ.ሲ.ስን ለመቃወም ወጥተው ሶስት ኣመት በሌላ ፍርድ ቤት የተፈረደባቸው እንዳሉ ከዚህ ቀደም መዘገባችን አይዘነጋም።

አቶ ማሙሸት አማረ የመኢአድ ሕጋዊው ፕሬዝዳንት ሲሆኑ ግንቦት 5 ቀን 2007 ከቤታቸው ሲወጡ በአገዛዙ ደህነቶች ታፍነው የተወሰዱ ሲሆን በጊዜው በእስር ላይ እንዳሉ የቀረበባቸው ክስ አይ.ሲ.ስን ለመቃወም መንግስት በጠራው ሰልፍ ላይ ተቃውሞ አስነስተሃል ሚል ሲሆን ለዚህም ክስ ሶስት የአገዛዙ ሀሰተኛ ምስክሮች ተሰምተዋል። አቶ ማሙሸት መከላከያ ባቀረቡበት ወቅት በዕለቱ ሰልፉ ላይ ሳይሆን ሕገ ወጥ ውሳኔ ወስኖ ከመኢአድ ጽ/ቤት በፖሊስ ያባረራቸውን ምርጫ ቦርድ ከሰው ፍርድ ቤት እንደነበሩ በማስረጃ ከልደታ ፍርድ ቤት አጽፈው ሲያቀርቡ ፍርድ ቤቱ ክሱ ተቋርጦ ይፈቱ ብሎ ማዘዙን ዘግበን ነበር።በጊዜው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይከበር ከእስር ቤት ወደ እስር ቤት የተወሰዱት አቶ ማሙሸት ለሁለተኛ ጊዜ አዲስ የፈጠራ ክስ ቀርቦባቸው ፍርድ ቤት ቀረቡ። ሁለተናው ፍርድ ቤት አቶ ማሙሸት በአይ.ሲስ. ልጆቻቸውን ያጡ ቤተሰቦችን ለቅሶ ደርሰው ወታቶችን ለአመጽ አደራጅተዋል የሚለው ላይ ተደጋጋኒ የጊዜ ቀጠሮ የቀረበውን ባለመቀበል በአምስት ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ ቢወስንም አገዛዙ ፍርድ ቤትን ሲፈልገው ማጥቂያ በመሆኑ ውሳኔውን ሳያከብር ላለፉት ሶስት ወራት ከእስር ቤት እስር ቤትና የይስሙላው ፍርድ ቤት እንደሌሎቹ የህሊና እስረኞች እየተጉላሉ ይገኛሉ።

ህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *