በፕሬዝዳንት ኦባማ የኢትዮጵያ ጉዞ ወቅት የአልሸባብ ሴል ሆነህ ለሽብር ጥቃት ተዘጋጅቷል በሚል የታሰሰረው ጋዜጠኛ ስለ ሁኔታው ጻፈ

ጋዜጠኛ ሀብታሙ ምናለ   ፕ/ት ኦባማ በአፍሪካ ህብረት ተገኝተው በተናገሩበት ወቅት
ጋዜጠኛ ሀብታሙ ምናለ               ፕ/ት ኦባማ በአፍሪካ ህብረት ተገኝተው በተናገሩበት ወቅት

ጋዜጠኛ ሀብታሙ ምናለ የቀዳሚ ገጽ ጋዜጣ ስራ አስኪያጅና የሚሊሊዮኖች ድምጽ ጋዜጣ ሪፖርተር ነበር። የፕ/ት ኦባማ የኢትዮጵያን ጉዞ ተከትሎ እነ ርዮት ዓለሙ በአስቸኳይ የተፈቱ ዕለት ማምሳውን በፈጠራ የአልሸባብ ሴል ሆነህ የሽብር ጥቃት ልትፈጽም ተዘጋጅተሃል በሚል ለ28 ቀናት ታስሮ ተፈቷል። ስለ እስር ቤት ሁኔታውና ስለተጠቀሰበት ክስ ከህብር ሬዲዮ ጋር ተወያይቷል። ከእስር ቤት መልስ ስለ ሁኔታው ዛሬ በገጹ ላይ ያሰፈረውን እንድታነቡት እንጋብዛለን።

ጥሩ አሟሟት ገዳዩን ያስመሰግናል! ከምን ጀምሬ በምን እንደምጨርስ አላውቅም ግን ሐምሌ 2 ከምሽቱ 5 ሰዓት ገደማ ደኅንነትና ፖሊሶች ቤታችንን ከበው መጣ የፍርድ ቤት ማዘዣ አሳዩኝ ብልም መቼ ጉዳዬ ብለውኝ በራችን ላይ ወደ 6 የሚሆኑ ፖሊሶች ውጭ ደግሞ ለቁጥር የሚታክቱ መሳሪያ የያዙ ፖሊሶች በተጠንቀቅ ቆመዋል ያለጥርጥር ከ20 ይበልጣሉ፡፡ አካባቢያችን ወዳለው ፖሊስ ጣቢያ እዛ ወሰዱኝ ጥያቄ የለም መልስ የለም በር ብቸ ከርችመው ለጥያቄዎቼ መልስ ሳይሰጡኝ አሳደሩኝ፡፡ በ2ኛው ቀን አምቼ አካባቢ ወዳለው የቦሌ ክ/ከ ፖሊስ መምሪያ ተወሰድኩ እዛም አስገብተውኝ ጥያቄ የለም ወደ እስር ቤት ማጎሪያ አስገቡኝ፡፡ ለምን አመጣችሁኝ በምን ተከሰስኩ ብል ሰሚ አጣሁ፡፡ በአንድ ነገር ብቻ ከፖሊሶች ጋር ሰፊ ጠብ ገጠምኩኝ ይኸውም ‹‹ማኅተብህን አውልቅ›› የሚል ሲሆን እንደማላወልቅ ከአሁን በኃላ የፈለጉትን ማምጣት እንደሚችሉ ስነግራቸው እርስ በእርስ ተጨቃጨቁ፡፡ አንደኛው ከወንበሩ ተነስቶ በንዴት አጠገቤ በመቆም ‹‹ማነህና አንተ የማታወልቀው›› ሲለኝ እኔም ‹‹ሀብታሙ ምናለ›› ስለው ብግን እያለ ‹‹ለምን ገባ ወጣ አናረገውም አላቸው (ወጣ ገባማለት በእስር ቆይታዬ እንደተረዳሁት እስኪበቃው በመግረፍ የተጠየቀውን እንዲያረግ ማስገደድ ነው፡፡) ከእዛ ሁለት ፖሊሶች በትግረኛ አወሩ ወይም ተጨቃጨቁ (አነጋገራቸው ስላልገባኝ ነው) ‹‹አንደኛው ማውለቅ እንዳለበት በትክክንገረው ››ሲል ሊላኛው ‹‹በቃ ለምን አርጎ አይገባም በእምነት ላይ መጨቃጨቅ ተገቢ አይመስለኝም! ›› አለው አውርተው ተስማሙ መሰለኝ መስቀሌንም ሳልበጥስ መግባት ቻልኩ፡፡ ስገባ አንድ ቤት ውስጥ አንድ ቋንቋ ብቻ የሚያወሩ ወደ 40 የሚጠጉ ሶማሌያውያን አገኘሁ፤ ሲያዩኝ ተጠጋጉልኝ ከበውኝ በጥያቄ አጣደፉኝ ‹‹ ሶማሌ ነህ›› አይደለሁም! ‹‹ ሙስሊም ነህ ›› አይደለሁም! ‹‹ታዲያ እንዴት ታሰርክ›› ሲሉኝ ከቤት ተይዤ ብቻ መምጣቴን እንደማውቅ ብቻ ነገርኳቸው አንዱ ጠጋ ብሎኝ ‹‹ እንዴት ታሰርክ ከሶማሌዎች ጋር ሥራ አብረህ ትሰራለህ?›› አልሰራም! አንድም ሱማሌ አላውቅም እናንተስ በምን ታሰራችሁ? ‹‹በሽብር›› ሲሉኝ ገርሞኝ ዝም አልኩ፡፡ በ4ኛው ቀን ተጠርቼ ክሴ የሽብር መሆኑን ግንኙነቴም ከአልሻባብ ጋር መሆኑን የእነሱም ህዋስ መሆኔን ኦባማ ሲመጣ ሽብር ለመፈጸም እንደተዘጋጀሁ ማስረጃዎች እንዳላቸው ገለጹልኝ፡፡ እኔም ተናድጄ አልሻባብ ጋር በምን ልገናኝ እችላለሁ? አንዳንዴ ክስ መመስረትና ሰውን ማጉላላት ፈሪ ማድረግ ይቻላል ወይ? ጠበቃ ተማም አባቡልጉ እንደተናገረው የክፍለ ዘመኑ ምርጥ ድራማ ያለው ትክክል ነው ክስም እኮ ወደ ሚመስል ነገር ሊጠጋ ይገባል!፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ጥሩ አሟሟት ገዳዩን ያስመሰግናል! ›› ያልኩት እነሱ ግን የማይመሰገን ገዳይ ሆኑ እንጂ በአጭሩ ክሱን እንደማልቀበል ተናገርኩ፡፡ የመጀመሪያው ቀን ሐምሌ 6 ቀን 2007ዓ.ም ‹‹ፍርድ ቤት›› ቀረብኩ መርማሪው ‹‹በሽብር የተከሰስኩ መሆኔንና ለምርመራ 14 ቀን እንደሚፈለግ ጠየቀ፡፡›› እኔም ለመጠርጠር የበቃሁበትን መነሻ ይነገረኝ ብልም ሰሚ የለም፡፡ ዳኛዋ ለአቃቤ ህጉ አንተ ጠይቀህማ ማን ከልክሎ በሚል አይነት ይመስላል 14 ቀኑን ወሰነችለት፡፡ እኔም ህጉ ስለሚፈቅድ ምንም አልተቃወምኩም ለጓደኞቼ በርቀት በምልክት ነግሬያቸው ወደ ጣቢያ ሄድኩ፡፡ በሁለተኛው ቀነ-ቀጠሮ ሐምሌ 20 ቀረብኩ፡፡ አሁንም አቃቤ ህጉ ምርመራውን እንዳልጨረሰና ተጨማሪ ቀን እንዲሰጠው ጠየቀ እኔም የዋስ መብቴ እንዲጠበቅ ብጠይቅም ሰሚ አጣሁ ከህይወቴ ላይ 10 ቀን ተጨልፎ ተሰጠው፡፡ አሁንም ወደ ማጎሪያዬ ሄድኩ፡፡ የፍርድ ቤት ቀነ ቀጠሮዬን እየጠበኩ ሳለሁ ሐምሌ 27 ማታ2፡30 የማደሪያ ቤታችን በር ተከፈተ እቃህን ያዝ! ስባል ወደ ሌላ እስር ቤት የሚያዘዋውሩኝ ነበር የመሰለኝ፤ ከዛ ከወጣሁ በኃላ ወደ ቤትህ መሄድ ትችላለህ! ተብዬ ያለምንም ዋስ ተሰናብቼ እንደዚህ ወጥቻለሁ፡፡ ‹‹ለጊዜው ነጻ ወጥቻለሁ›› ‹‹ለጊዜው ነጻ ብወጣም›› ነገም ጎትተው ሊከቱኝ ቢችሉም አናፈገፍግም! አናፈገፍግም! አናፈገፍግም! ምክንያቱም ለስለት ያሉት ገላ አያምም! ከተያዝኩበት ቀን ጀምሮ የደከማችሁልኝ የተስፋ ኢየሩሳሌም ሰ/ት/ቤት አባላት፣ ጓደኞቼ፣ የአካባቢዬ ነዋሪዎች፣ የቦሌ ሚካኤል ህዝብ እንዲሁም በጋዜጣም ሆነ በተለያየ መልኩ መታሰሬን ሰምታችሁ እስር ቤት ድረስ መጥታችሁ የጠየቃችሁኝ በመሉ ከልቤ አመሰግናለሁ፡፡ ስማችሁን ባልጠራ ግን የሚከፋኝ ስለመሰለኝ ነው አቶ መስፍን በዳዳ፣ዮሐንስ፣ ዘላለም፣ይትባረክ ፣ፍፁም ፣ ሀብቴ ሞክሼ፣ኢርሚያስ ፣ ማስሬ፣ሜቲ፣ ቃለክርስቶስ ፣ፋንትሽ …………………ሊሎችም መቼም ለእኔ የሆናችሁትን አልረሳም!

     ህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *