Hiber Radio: ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ፣አናኒያ ሶሪና ዳንኤል ሺበሺ ማእከላዊ መታሰራቸው ታወቀ፣ የኮማንድ ፖስቱን አዋጅ በመቃወም ፎቶ ተነስተው መለጠፋቸው የወንጀል ሰበብ ሆኗል፣ከተያዙ በሁዋላ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ጥርጣሬ አለ

elias-daniel-anania-soori-001

በማህበራዊ ሚዲያ በአገር ቤት ያለውን የግፍ አገዛዝ የተለያዩ የአፈነ እርምጃዎች ሲያጋልጡና ሲተቹ የቆዩት ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ፣ጋዜጠና አናኒአ ሶሪ እና የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ ምክትል የድርጅት ጉዳይ ሀላፊው ዳንኤል ሺበሺ ዛሬ አርብ ህዳር 9 ቀን 2009 ከያሉበት በደህነቶች ታፍነው ወደ ማዕከላዊ መወሰደዳቸው ታውቋል።ከተወሰዱ በሁዋላ ወዲያው አካላዊ ጥቃት ሳይፈጸምባቸው እንዳልቀረ ጥርጣሬ አለ።ስለ ጉዳዩ ቤተሰብም ሆነ ወዳጅ ዘመድ ቀርቦ ማጣራት አልተቻለም።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ የኦሮሞ ሰላማዊ ታጋዮች ኣርማ እየተደረገ የሚጣወቀውን በሰላም እጃቸውን ወደ ላይ በማድረግ አመሳቅለው በአንድነት ፎቶ በመነሳት ያንኑ በመለጠፍ ወንጀል ሰርተዋል ሲል አገዛዙ ሊወነጅል ቢሞክርም ሰሞኑን ጭምር ተደጋጋሚ ክትትል እንደነበረባቸው ለማወቅ ተችሏል።

ዳንኤል ሺበሺ ከሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወር በላይ ከእነ ሀብታሙ አያሌው ጋር በግፍ ታስሮ የተፈታና ዛሬም ድረስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚመላለስ ሲሆን በቅርቡ ፍርድ ቤቱ በቀጠሮ ሲሄዱ <<ከመዝገቡ ላይ ከደህነት የመጣው ማስረጃ ጠፍቷል>> በሚል ሰበብ ቀጠሮ መራዘሙን በመግለጽ አሁንስ ምን እንደምል ግራ ይገባኛል ሲል ጉዳዩን ተጭቷል።

ከአስቸኳይ አዋጁም በሁዋላ መናገርና መጻፍ ያላቆሙት ጋዜጠኛ ኤልአስ ገብሩ፣አናኒያ ሶሪና ከዳንኤል ሺበሺ በተጨማሪ ዛሬ የሕወሓት አገዛዝ ኮማንድ ፖስት የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ አባላትን በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች በዘመቻ ማሰር መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል።

ጋዜጠኛ ኤልያስ በቅርቡ ኮማንድ ፖስቱን ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ቃለ መጠይቅ ሰጥተህ ተችተሃል በሚል የታሰረውን ጦማሪ በፍቃዱ ሀይሉን ጎብኝቶ መዘገቡ ይታወሳል።

ጋዜጠኛ አናኒያ ሶሪ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀደም ብሎ በሕወሓት ልሳን ራዲዮ ፋና የውይይት መድረክ ቀርቦ በግልጽ ስርኣቱ በስብሷል፣በሙስና ነቅዟል በሚል በተቸበት ወቅት ካድሬ ጋዜጠናው ጭምር በተደጋጋሚ በንዴት ሊያቋርጠው ሲሞክር በዚያው ሰሞን እስር እንደሚጠብቀው ብዙዎች ግምታቸውን ሲሰጡ ቆይተዋል።

በአሁኑ ወቅት በማዕከላዊ የሚገኙት እነ ጋዜጠና ኤልአስ ገብሩ አካላዊ ጥቃት እንደገቡ ተፈጽሞባቸዋል የሚባለውን መረጃ ለማጣራት ቤተሰብም ሆነ ሊጠይቁ የሄዱ ለማየት አለመቻላቸውን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።

ኮማንድ ፖስቱ(የሕወሓት ወታደራዊ እና የደህነት አመራር) ባሳለፈው ትዕዛዝ ከአዲስ አበባ፣ከኦሮሚያ፣ከአማራና ከደቡብ ክልል ብቻ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ከ11 ሺህ በላይ ንጹሃንን አስሬያለሁ ያለ ቢሆንም ቁርሩ ከ15 ሺህ በላይ እንደሚሆን የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የታሰሩ ሰዎች በተለይ በልዩ ልዩ እስር ቤቶችና ወታደራዊ ካምፖች የሚገኙ ከፍተና አካላዊ ጥቃት እየተፈጸመባቸው ሲሆን ይህን አሰቃቂ ግፍ ስርዓቱ ተሃድሶ እያለ በመግለጽ ላይ ይገኛል።

ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *