Hiber Radio: ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ፣አናኒያ ሶሪና ዳንኤል ሺበሺ ገርጂ ፖሊስ ጣቢያ ተገኙ፣ ፎቶ ተነስተው መለጠፋቸው የወንጀል ሰበብ ሆኗል

elias-daniel-anania-soori-001

በማህበራዊ ሚዲያ በአገር ቤት ያለውን የግፍ አገዛዝ የተለያዩ የአፈነ እርምጃዎች ሲያጋልጡና ሲተቹ የቆዩት ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ፣ጋዜጠኛ አናኒአ ሶሪ እና የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ ምክትል የድርጅት ጉዳይ ሀላፊው ዳንኤል ሺበሺ ዛሬ አርብ ህዳር 9 ቀን 2009 ከያሉበት በደህነቶች ታፍነው ወደ ማዕከላዊ ተወስደዋል ተብሎ ቤተሰብ ማዕከላዊ ድረስ ሄደው ሊያገኙዋቸው ሳይችሉ ባይችሉም በተደረገ ማጣራት በአሁኑ ወቅት በገርጂ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙ ሲሆን አካላዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል የሚባለውን ማጣራት አለመቻሉን ለማወቅ ተችሏል። ኮማንድ ፖስቱ ነው ያሰራችሁ ተብለው በአደራ እስር ላይ በጣቢያ የሚገኙ ሲሆን ፍርድ ቤት ይቅረቡ አይቅረቡ ለማወቅ አልተቻለም።

ከታሰሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ የኦሮሞ ሰላማዊ ታጋዮች ዓርማ እየተደረገ የሚታወቀውን በሰላም እጃቸውን ወደ ላይ በማድረግ አመሳቅለው በአንድነት ፎቶ በመነሳት ያንኑ በመለጠፍ ወንጀል ሰርተዋል ሲል አገዛዙ ሊወነጅል ቢሞክርም ሰሞኑን ጭምር ተደጋጋሚ ክትትል እንደነበረባቸው አስቀድሞ መዘገባችን ይታወሳል።

ዳንኤል ሺበሺ ከሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወር በላይ ከእነ ሀብታሙ አያሌው ጋር በግፍ ታስሮ የተፈታና ዛሬም ድረስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚመላለስ ሲሆን በቅርቡ ፍርድ ቤቱ በቀጠሮ ሲሄዱ <<ከመዝገቡ ላይ ከደህነት የመጣው ማስረጃ ጠፍቷል>> በሚል ሰበብ ቀጠሮ መራዘሙን በመግለጽ አሁንስ ምን እንደምል ግራ ይገባኛል ሲል ጉዳዩን ተችቷል።

ከአስቸኳይ አዋጁም በሁዋላ መናገርና መጻፍ ያላቆሙት ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ፣አናኒያ ሶሪና ከዳንኤል ሺበሺ በተጨማሪ ዛሬ የሕወሓት አገዛዝ ኮማንድ ፖስት የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ አባላትን በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች በዘመቻ ማሰር መጀመሩን ለማወቅ አስቀድሞ የዘገብን ሲሆን በዚህ ዘመቻ በርካቶች በመታሰር ላይ ናቸው።

ጋዜጠኛ ኤልያስ በቅርቡ ኮማንድ ፖስቱን ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ቃለ መጠይቅ ሰጥተህ ተችተሃል በሚል የታሰረውን ጦማሪ በፍቃዱ ሀይሉን ጎብኝቶ መዘገቡ ይታወሳል።

ጋዜጠኛ አናኒያ ሶሪ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀደም ብሎ በሕወሓት ልሳን ራዲዮ ፋና የውይይት መድረክ ቀርቦ በግልጽ ስርኣቱ በስብሷል፣በሙስና ነቅዟል በሚል በተቸበት ወቅት ካድሬ ጋዜጠኛው ጭምር በተደጋጋሚ በንዴት ሊያቋርጠው ሲሞክር በዚያው ሰሞን እስር እንደሚጠብቀው ብዙዎች ግምታቸውን ሲሰጡ ቆይተዋል።

ኮማንድ ፖስቱ(የሕወሓት ወታደራዊ እና የደህነት አመራር) ባሳለፈው ትዕዛዝ ከአዲስ አበባ፣ከኦሮሚያ፣ከአማራና ከደቡብ ክልል ብቻ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ከ11 ሺህ በላይ ንጹሃንን አስሬያለሁ ያለ ቢሆንም ቁርሩ ከ15 ሺህ በላይ እንደሚሆን የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የታሰሩ ሰዎች በተለይ በልዩ ልዩ እስር ቤቶችና ወታደራዊ ካምፖች የሚገኙ ከፍተና አካላዊ ጥቃት እየተፈጸመባቸው ሲሆን ይህን አሰቃቂ ግፍ ስርዓቱ ተሃድሶ እያለ በመግለጽ ላይ ይገኛል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *