Hiber Radio: የሙያ አጋሮቼን ባሰብኩ ጊዜ አለቀስኩ! በጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋው

ከላይ  ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ተመስገን ደሳለኝ፣ከታች ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው እና ጋዜጠና አበበ ውቤ
ከላይ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ተመስገን ደሳለኝ፣ከታች ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው እና ጋዜጠና አበበ ውቤ

ዕከለ ሌሊት ካለፈ ቆዬ፤ በእርግጥ ሳይነጋ እየመሸ ስለሆንኩ የቀንና የሌሊት ድንበር በሌለበት አገር ነው ያለሁት፡፡ ዛሬ የኤልያስ ገብሩንና የአናንያ ሦሪን መታሰር ሰማሁና ምን የቀረ ጋዜጠኛ አለ? በማለት ኅሊናየን ጥያቄ አቀረብኩለት፤ ምንም ነበር መልሴ፡፡

በጋዜጠኛነት በሠራሁባቸው ጥቂት ዓመታት ብዙ ወዳጆቼ ወይ እንደኔ ተሰደዋል፤ አሊያም ወደ ቃሊቲ ገብተዋል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የነጻው ሚዲያ ምኅዳር ካበቃለት ቆየ፡፡ ግን ያሳዝናል፤ ያናድድማል!

  1. ኤልያስ ገብሩና አናንያ ሦሪ፤ በምርጫ 2007 ዓ.ም. ወደ ሃያ የሚጠጉ ጋዜጠኞች ወደ ጎረቤት አገር ሲሰደዱ ከኤልያስ ገብሩና ከአናንያ ሦሪ ጋር ደጋግመን በመገናኘት ‹‹ይህን ጊዜ ሳንታሰር እንዴት እንለፈው?›› እያልን ደጋግመን ተነጋገርን፤ ላለመሰደድ ቆርጠን ምናልባት ምርጫ ካለፈ በኋላ ተመልሰን ሕትመት ለመጀመር አቀድን፡፡ የምንችለውን ያክል አደረግን፡፡ እኔ ተሰደድኩ፤ እነ ኤልያስና አናንያ ሕትመት አቆሙና ዛሬ መታሰራቸውን ሰማሁ፡፡ በነገራችን ላይ አናንያ ሦሪ በፋና ሬዲዮ ብቻውን የዐማራ ሕዝብ እየደረሰበት ያለውን አደጋ በድፍረት ሲግታቸው የማያስታውስ ያለ አይመስለኝም፡፡

2. ጌታቸው ወርቁ- በ2003 ዓ.ም. የኢትዮ ምኅዳር ጋዜጣ ስትመሠረት ጀምሮ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁን አውቀዋለሁ፡፡ የኢትዮ ምኅዳር ጋዜጣ ከ2ኛዋ ዕትም ጀምሮ ከሁለት ዓመታት በላይ የእኔ አንድ ጽሑፍ አብሮ ይኖራል፡፡ ኢትዮ ምኅዳር ጋዜጣ ላይ ነው እኔ ጽሑፍ በቋሚነት መጻፍ የጀመርኩት፡፡ ኢትዮ ምኅዳር ጋዜጣ በመተከልና በከማሽ የዐማራ ገበሬዎች ሲፈናቀሉ ተደጋጋሚ ጽሑፎችን ስልክ ይታተምልኝ ነበር፤ ይህም ከሌሎች በበለጠ ለኢትዮ ምኅዳር የነበረኝ ፍቅር የላቀ ነው፤ ምን ያደርጋል ጌታቸው ወርቁ የማርያም ቤተ ክርስቲያን ላይ የትግራይ ሙሰኛ ቀሳውስት የሚያደርጉትን የሙስና ቅሌትና ዘረኝነት በማተሟ ብቻ ባለጊዜዎቹ ጋዜጠዋን ዘግተው ለአንድ ዓመት ቃሊቲ አስገቡት፡፡ የጌታቸውን የፍርድ ሒደት ከአንድ ዓመት በላይ ስከታተለው ቆይቻለሁ፡፡

3. በፈቃዱ ኃይሉ- አብዛኛዎቹ የዞን ፱ ጦማሪዎች ጋር የተዋወቅኩት ከተፈቱ በኋላ ነበር፡፡ እነ በፈቃዱ ‹‹ውይይት›› የምትባል መጽሔት ጀምረው ተወዳጅ ሆናላቸው ነበር፤ ግን ይኼው ከታሰረ ሳምንት አለፈው፡፡

4. አበበ ውቤ፤ የቀለም ቀንድ ጋዜጣ ላይ አብሮኝ የደከመ ወንድሜ ነው፤ አበበ የቀለም ቀንድ ጋዜጣን ለማሳደግ የደከመውን ድካም እዚህ ላይ መዘርዘር አልችልም፡፡ አቤ ባይኖር እኔ ጋር ባይኖር ኖሮ በገቢዎች ችግር ብቻ ጋዜጠዋ በአንድ ወር ትዘጋ ነበር፡፡ ይኼው አበበ ከጥቅምት 9 ቀን 2009 ጀምሮ በር ተዘግቶበታል፡፡

5. ጌታቸው ሽፈራው- የጌታቸው ሽፈራውን ጉዳይ ከጋዜጠኛ በላይ ማናዬ የላቀ የሚገልጽ ሰው የለም፡፡ አሁን ባለሁበት አገርም የጥሩ ጓደኛነት ምሳሌ የማደረግው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራውንና ጋዜጠኛ በላይ ማናየን ነው፡፡ ጌታቸው ጥሩ ወዳጄ ነበር፡፡ የጌታቸውን ቅንነትና ታታሪነት ግን ብዙ ሳልጠቀምበት ቃሊቲ ከወረደ አንድ ዓመት አለፈው፡፡ ጌቾ የሰው ልክ፡፡

6. ውብሸት ታየ፤ ዝዋይ ከወረዳ (ካልተሳሳትኩ) ስድስት ዓመት አልፎታል፤ ጋዜጠኛ ውብሸት ታየ የ14 ዓመት እስር ተበይኖበት የጋዜጣው ባለቤት ግን ‹‹ከምርጦች ወገን›› በመሆኑ በደስታ በአዲስ አበባ ይኖራል፤ እንዲያውም ከእርሱ በላይ የሥርዓቱ የቅርብ ሰው የለም፡፡ ውብሸት የፊቼ ሰላሌ ልጅ ነው፡፡ የማውቀው ከታሠረ ነው፡፡ ይህን ያክል ዓመት ታስሮ እንኳ ያለው ጥንካሬ ይገርመኛል፡፡ ጥቂት ቀናት ዝዋይ ሒጄ ስለጠየቅኩት ከተሰደድኩ በኋላ ‹‹ሥጦታ›› አዘጋጅቶልኝ እንደነበር በጓደኛየ በኩል ሰማሁ፡፡ የውብሸት ባለቤት ጥንካሬ ይገርመኛል፡፡ ውብሸትን በተመለከተ ብዙ የምጸፈው ይኖራል፤ እኔ አሁን እርሱን መጠየቅ አልችልም- ግን የሚጠይቅልኝ ሰው መኖሩ ቢያንስ በትንሹም ቢሆን ደስ እንዲለኝ ያደርጋል፡፡

7.ተመስገን ደሳለኝ፤ ዝዋይ ከሔደ ሦስት ዓመት አለፈው፤ በአመክሮ እንኳ እንዳይፈታ ተከለከለ፡፡ ተሜን ስትጠይቁት ‹‹ከእስር በኋላ አገራችን እንዴት ልንታደጋት እንችላለን?›› ስለሚል እቅድ ነው የሚያወራችሁ፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ሳገኘው ወገቡንና ጆሮው አካባቢ መታመሙን እና አርሱን ሆን ብለው እርሱን የሚከተሉ ደኅንነቶች ከክፍሉ እንደነመደቡ ነገረኝ፡፡ በሕይወቱ ላይ አንዣቦ የነበረውን አደጋ በተሜ ፊት ላይ ከሚነበበው እልህ ያለበት የደፈረሰ ስሜት አንብቤ ነበር፡፡ ተመስገን ከእርሱ ይልቅ ስለ እስክንድር ነጋ አጥብቆ ያስባል፡፡

8.እስክንድር ነጋ፤ እስካሁን በአካል ለማወቅ አልታደልኩም፡፡ ለመጠየቅ ደጋግሜ ሞክሬ አልተሳካልኝም፡፡ አንድ ጊዜ ተመስገን ሒደህ አግኘው ብሎ አዞኝ ነበር የሄድኩት፡፡ ግን መጠየቅ የማልችል ሆነ፡፡ እስክንድርን ከባለቤቱ ሰርካለም ፋሲል እናት እና ተፈራ ከተባለ ጓደኛው ውጭ ማንም ብዙ ጊዜ እንዲጠይቀው አይፈቀድለትም፡፡ የእስክንድርን ጉዳይ ለማጣራት በጓደኛው በኩል ነበር፡፡ እስክንድር (ብርቱው ሰው) መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ ብዙ ጊዜ ማንበብም ይከለከል ነበር፡፡

የወያኔዋ ኢትዮጵያ እንግዲህ ይህች ነች!! የሙያ አጋሮቼን ባሰብኩ ጊዜ አለቀስኩ፤ ለቅሦየ ግን እልህና ንዴት የተቀላቀለበት ነው፡፡

ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *