Hiber Radio: የላስ ቬጋስ ፖሊስ የዕሁዱን ግድያ የፈጸመው ግለሰብ አስቀድሞ ዳውንታውን በተደረገ ኮንሰርት ወቅት ክፍል ተከራይቶ እንደነበር ገለጸ ፣የቪዲዮ መረጃ ፖሊስ እጅ ገብቷል

(ህብር ሬዲዮ-ላስ ቬጋስ) የላስ ቬጋሱን የዕሁድ የሀርቨስት ሩት 91 የአገረሰብ የሙዚቃ ኮንሰርት ከ22 ሺህ በላይ ታዳሚዎች ላይ ካለበት የማንዳላቤ 32ተኛ የሆቴል ክፍል የ64 ዓመቱ  ስቲቨን ፓዶክ በከፈተው ተኩስ 58 ንጹሃንን ገሎ ከ527 ከማቁሰሉ በፊት <<ላይፍ ኢዝ ቢዩቲፉል>> የተሰነ ስያሜ ይዞ ከሴምቴምበር 22 እስከ 25 በዳውንታውን በተደረገው የሙዚቃ ኮንሰርት ወቅት ክፍል ተከራይቶ እንደነበር የላስ ቬጋስ ፖሊስ ዋና አዛዥ ሸሪፍ ጆሴፍ ላምባርዶ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ ገለጹ።

የፖሊስ ሸሪፉ ጆሴፍ ላምባርዶ እንደገለጹት የዕሁዱን ጭፍጨፋ ያደረሰው ስቲቨን ፓዶክ በዳውንታውን ቀደም ብሎ ተደርጎ በነበረው የሙዚቃ ኮንሰርት ወቅት በስፍራው ሳለ የነበረውን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ቪዲዮ መርማሪዎች እጅ መግባቱን በመግለጫው ወቅት ለዜና ሰዎች ገልጸዋል።በአሜሪካ ታሪክ በአንድ ጊዜ በተከፈተ ተኩስ ይህን መሰሉ ጭፍጨፋ የመጀመሪያ መሆኑን ጠቅሰው ምርመራው መቀጠሉን አመልከተዋል።ፖሊስ የመጀመሪአው ተኩስ ከተከፈተበት 10፤05 ፒኤም ጀምሮ በየደረጃው ተጠርታሪው ክፍል በ75ተኛው ደቂቃ እስኪገባ የነበረውን ሂደት በየደረጃው በመግለቻው ወቅት አብራርተዋል።

የሜትሮ ፖሊስ በሰጠው በዚህ መግለጫ ተጠርጣሪው በክፍሉና ከክፍሉ ውጭ የነበረውን ሁኔታ የሚቆጣጠርበት ሁለት ካሜራ መገኘቱን የገለጹ ሲሆን ካሜራዎቹ አንዳቸውም አለመቅረጻቸው ይፋ አድርገዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዕሁዱን ጭፍጨፋ ያካሄደው ግለሰብ የሴት ጓደኛ ማሪሎ ዳንሌይ  ከፊሊፒንስ የመጣች ሲሆን በጠበቃዋ በኩል በሰጠችው መግለጫ ስለ ግድያ ዓላማው ምንም እንደማታውቅ የገለጸች ሲሆን ወደ ፊሊፒን ከሔደች በሁዋላ ለቤተሰቦቿ ለቤት መግዣ ብሎ ገንዘብ እንደላከላት ገልጻለች። ግድአውን የፈጸመው ስቲቨን ፓዶክ ጋር በኔቫዳ መስኪት አብራ የምትኖረው ይህቺው ሴት በጽሁፍ በሰጠችው በዚህ መግለጫ በምርመራ ሂደቱ ተባባሪ መሆኑዋን ጠቅሳ አስቀድሞ ፊሊፒንም በነበረችበት ወቅት የአሜሪካ ፌዲራል መርማሪዎች ኤፍቢአይ እና የላስ ቬጋስ ፖሊስ ደውለው እንዳናገሯት ጠበቃዋ ገልጿል።

የዕሁዱን ጭፍጨፋ ያደረሰው ስቲቨን ፓዶክ የፖለቲካም ሆነ ሀይማኖታዊ ኣላማ የለውም ቢባልም ዛሬም ድረስ ዋና ዓላማው ምን እንደነበር አልታወቀም።

ከ58ቱ ሟቾች አንዱ የሆነው የላስ ቬጋስ ፖሊስ ባልደረባ አስከሬን  ወደሚያርፍበት  ዳውንታውን ፓልም ሞርቸሪ በፖሊስ ወታደራዊ አጀብና በክብር ብዙዎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተሸኝቷል። በነገው ዕለት በ6ፒ.ኤም ኦፊሰሩን ለማሰብ በሚደረገው የሻማ ማብራት ስነ ስርዓት በፖሊስ መታሰቢያ ፓርክ 3250 ሜትሮ አካዳሚ ዌይ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕና ባለቤታቸው ሜሌኒያ ትራምፕ ዛሬ በቬጋስ ቆይታ አድርገው ተመልሰዋል።ትራምፕ በሰጡት መግለጫ አደጋው በደረሰበት ወቅት በሙዚቃ ኮንሰርቱ ላይ ለመዝናናት ተገኝቶ የሰው ሕይወት ለማዳን ጥረት ሲያደርግ ሕይወቱ ያለፈውን የላስ ቬጋስ ፖሊስ ባልደረባ የሆነውን ቻርልስተን ሀርትፊልድ የላቀ ጀብዱ መፈጸሙንና ታላቅ ሰው መሆኑን ገልጸዋል። ትራምፕና ባለቤታቸው በአደጋው ወቅት ፈጥነው የተገኙ የጸጥታ አስከባሪዎችን፣በሆስፒታል ተገኝተው ሀኪሞችንና የተጎጂ ቤተሰቦችን ማጽናናታቸውንና ፖለቲከኞች ጋር መወያየታቸው ተመልክቷል።

ፖሊስ ትላንት በሰጠው መግለጫ የአደጋው ምርመራ እተካሄደና ትዕግስት እንደሚያስፈልግ መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል። ከተጠርጣሪው ከተከራየው የሆቴል ክፍል እና ከቤቱ  የተገኘውን ጨምሮ 47 መሳሪያ እንደተኘበት ሲ.ኤን.ኤን ከላስ ቬጋስ በቀጥታ ዘግቧል። ለፖሊስም ሆነ ለኤፍ.ቢ.አይ ተጨማሪ መረጃ ስለ ጥቃት አድራሹ ያለው መረጃ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል።ለላስ ቬጋስ ፖሊስ ተጨማሪ መረጃ ያለው በስልክ ቁጥር 702 828 3111 ወይም በቬጋስ ለሚኖሩ በ311 መደወል ለተጎጂዎች ለመርዳትም የጎፈንድ ሚ አካውንት ተከፍቶ እርዳታ እየተሰባሰበ ነው።

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ  5639993994 ወይም 563999-3988 ወይም 712-432-8451 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *