በሊቢያ የደረሰውን ግድያ ለመቃወም ወጥተው በፌዴራል ፖሊስ ከተደበደቡት አንዱ አዛውንት ሞቱ

police_addis_003በሊቢያ የደረሰውን ግድያ ለመቃወም ወጥተው በፌዴራል ፖሊስ ከተደበደቡት አንዱ አዛውንት ሞቱ

በኢትዮጵያውያን ላይ በሊቢያ የተወሰደውን የግፍ እርምጃና ለእርምጃው ስርዓቱ ያሳየውን ግዴለሽነት  ለመቃወምና ሐዘናቸውን ለመግለጽ አዲስ አበባ ከወጡት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰልፈኞች የፌዴራል ፖሊስ በወሰደው የድብደባ እርምጃ ቁትራቸው በውል ካልታወቀ በርካታ ተጎጂዎች  አንዱ በደረሰባቸው ድብደባ በሆስፒታል ሲታከሙ ቆይተው ትላንት ሕይወታቸው ማለፉን ቤተሰቦቻቸው አስታወቁ።

በአዲስ አበባ በተለምዶ ዑራኤል አካባቢ የሚኖሩት አቶ ሔኖክ ስዩም የተባሉ የ55 ዓመት አዛውንት በወቅቱ በደረሰባቸው ድብደባ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሕይወታቸው ትላንት ማለፉን እና ሕዝቡ ቤተሰቦቻቸውን እንዲያጽናና ጭምር እየተጠየቀ ይገኛል።

የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ከሆኑት አንዱ ይድነቃቸው ከበደ በበኩሉ የአቶ ሔኖክ ስዩም ማረፍን ቤተሰቦቻቸው ማሳወቃቸውን ገልጾ እሱም በበኩሉ ሕዝቡ እንዲያጽናናቸው ጠይቋል።

ባለፈው ሐሙስ አገዛዙ በጠራው የሊቢያን ጥቃት የመቃወሚያ ሰልፍ ላይ ካድሬዎቹን መፈክር አሲዞ ሰማያዊ ፓርቲን ለመቃወም ቢሞክርም ሕዝቡ <<..መንግስት የሌለው ኢትዮጵአ ብቻ ነው!>> <<የቤት አንበሳ የውጭ ሬሳ >> << ወንድነታችሁ በአይ.ሲስ ላይ ይታይ>><<ይሌአል ዘንድሮ የወያኔ ኑሮ!>> << ኢትዮጵያ አገሬ ያስደፈረሽ ይውደም!>> እና ሌሎችንም ስሜት ቀስቃሽ የተቃውሞ ድምጾቹን በይፋ አስተጋብቷል። ለሐዘን የወጣው ሕዝብ ቁጣውን መግለጹን ተከትሎ የስርኣቱ የፌዴራል ፖሊሶች በወሰዱት ድብደባ <<ወያኔ የአገር ቤት አይ.ሲስ>> የሚል ተቃውሞ ጭምር በሰልፉ ላይ ተደምጧል። ተቃውሞውን ተከትሎ በተወሰደ ድብደባ በርካቶች የተጎዱ ሲሆን በተቃውሞወ ዕለትና ከዚያም በሁዋላ ወጣቶች ከተሌኤዩ የከተማዋ አካባቢዎች እየታፈሱ እየተደበደቡ መታሰራቸው ታውቋል።

በህብር ሬዲዮ አስቀድሞ የአገር ቤቱን ተቃውሞ መዘገቡ ይታወሳል። ህብር ሬዲዮን በየቀኑ በድህረ ገጻችንና በዘሐበሻ እንዲሁም በስልክ 7124328451 ደውሎ ሁለትን በመጫን ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *